ቴሌግራም ባለፉት አራት ወራት ምን አይነት ለውጦችን ለማድረግ ተገደደ?
የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች እንዳይሰራጩ ከሚቆጣጠረው አለማቀፍ ኩባንያ ጋር ለመስራት ተስማምቷል
ከ950 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም የ"ወንጀለኞችና እጽ አዘዋዋሪዎች መደበቂያ ሆኗል" የሚል ክስ ይቀርብበታል
ቴሌግራም የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች እንዳይሰራጩ ከሚቆጣጠረው አለማቀፍ ኩባንያ ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ።
ታዋቂው የመልዕክት መለዋወጫ ለአመታት ሲቀርብለት የነበረውን ጥያቄ ተቀብሎ "ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን" ከተሰኘው ተቋም ጋር ለመስራት መስማማቱን አስታውቋል።
"አይደብሊውኤፍ" የህጻናት ወሲባዊ ቪዲዮዎች እና ምስሎችን የሚለይና እንዳይሰራጩ የሚያፍግድ ስርአት ያለው ሲሆን፥ ከተለያዩ የኦንላይን አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ይሰራል።
ከ950 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚ ያለው ቴሌግራም ቅድሚያ ለደንበኞቼ ግላዊ ነጻነትና ደህንነት እሰጣለሁ በሚል እንደ "አይደብሊውኤፍ" ካሉ ተቋማት ሲቀርቡለት የነበሩ ጥያቄዎችን ውድቅ አድርጓል።
መተግበሪያው የበዛ ነጻነት መስጠቱ የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች በፍጥነት እንዲሰራጩ አድርጓል፤ የወንጀለኞችና የእጽ አዘዋዋሪዎች መደበቂያ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል የሚሉ ክሶችም ሲቀርቡበት መቆየቱን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
መስራቹና ዋና ስራ አስፈጻሚው ፓቨል ዱሮቭ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በቁጥጥር ስር ውሎ ክሶች ከተመሰረቱበት በኋላ ግን የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ተገዷል።
የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች ስርጭትን የሚያግደው ተቋም "ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን" የቴሌግራም ውሳኔ ጥሩ ጅምር ቢሆንም "ገና ረጅም ጉዞ አለው" ሲል ገልጿል።
የቴሌግራም ጊዜያዊ ስራ አስፈጻሚ ደሬክ ሂል መተግበሪያው "አይደብሊውኤፍ"ን በመቀላቀሉ የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች እንዳይጋሩ ያደርጋል ብለዋል።
የቴሌግራም ባለቤት ፓቨል ዱሮቭ በነሃሴ ወር ከፓሪስ በስተሰሜን በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሲውል መተግበሪያው የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች እና የእጽ ዝውውር ማከናወኛ ሆኗል በሚል ለሚቀርቡ ክሶች ምላሽ አይሰጥም፤ ከህግ አስከባሪዎች ጋርም አይተባበርም ሲል ተወቅሷል።
የፈረንሳይ ዳኞች የ40 አመቱ ዱሮቭ ከሀገሪቱ እንዳይወጣ ማገዳቸውን ተከትሎ ቴሌግራም ለአመታት ጠንካራ አቋም ይዞባቸው ከነበሩ ጉዳዮች ሸርተት ብሏል።
የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ስልክ ቁጥር ለህግ አካላት አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል።
በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሰዎችን የሚጠቁመው "ፒፕል ኒርባይ" የተሰኘ ፊቸሩንም የመረጃ መንታፊዎች ኢላማ ይሆናል በሚል ማስወገዱ ይታወሳል።
መተግበሪያው ከመርሁ ውጪ የሆኑ ምን ያህል ይዘቶችን እንዳስወገደ የሚጠቁም ሪፖርትንም በየጊዜው ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ደርሷል።
ቴሌግራም የአለማቀፉ የህጻናት ወሲባዊ ይዘቶች ተቆጣጣሪ ተቋም አባል ከመሆኑ በፊት በየወሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ይዘቶችን በራሱ ስርአት አማካኝነት ለይቶ ሲያስወግድ መቆየቱን በመጥቀስ "አይደብሊውኤፍ"ን መቀላቀሉ ይህንኑ ጥረቱን እንደሚያግዝ ገልጿል።
"ትችት የበዛበትን ቴሌግራም ወደቀደመ ክብሩ እንመልሰዋለን" የሚሉት መስራቹና ስራ አሰፈጻሚው ፓቨል ዱሮቭ እየተደረጉ የሚገኙ ማሻሻያዎች የሚነሱትን ቅሬታዎች እንደሚቀርፉ ያምናሉ።