ትራምፕ አልያም ሃሪስን ለድል የሚያበቁ 10 ምክንያቶች
የአሜሪካ ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ፈተና ለትራምፕ፤ ፅንስን ማቋረጥ የሚፈቅደው ህግ ደግሞ ለሃሪስ በምርጫው ማሸነፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል
የስደተኞች ጉዳይና አሜሪካ ለውጭ ሀገራት ጦርነቶች የምታወጣው ወጪን በተመለከተ ተፎካካሪዎቹ ያነሷቸው ነጥቦችም ዋይትሀውስ ለመዝለቅ ወሳኝ ናቸው ተብሏል
አሜሪካውያን ለቀጣይ አራት አመታት የሚመራቸውን/የምትመራቸውን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ሰአታት ቀርቷቸዋል።
የቅድመ ውጤት ትንበያዎች ሃሪስ በአነስተኛ ልዩነት እንደምታሸንፍ ቢያመላክቱም ተፎካካሪዎቹ የምርጫውን ውጤት በሚወስኑ ግዛቶች የመጨረሻ ቅስቀሳቸውን አድርገዋል።
በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካማላ ሀሪስ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን፥ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በምርጫ ተሸንፎ ዳግም በመወዳደርና በማሸነፍ ከ130 አመት በኋላ ታሪክ ለመስራት ትንቅንቅ ውስጥ ናቸው።
ቢቢሲ ዶናልድ ትራምፕ አልያም ካማላ ሃሪስን ለታሪካዊ ድል ሊያበቁ የሚችሉ 10 ምክንያቶችን ዘርዝሯል።
ትራምፕ ሊያሸንፉ ይችላሉ ምክንያቱም፦
1. ስልጣን ላይ ስላልሆኑ
ለመራጮች የኢኮኖሚ ጉዳይ ቀዳሚው አጀንዳ ነው። አሜሪካውያን በባይደን አስተዳደር የስራ አጥነት መስፋፋቱንና በየቀኑ በሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ መፈተናቸውን ይገልፃሉ።
በ2024 በተለያዩ የአለም ክፍሎች በተደረጉ ምርጫዎች በስልጣን ላይ ያለ መንግስት የተነሳው ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑን መራጮች ሲያነሱ ተሰምቷል።
አሜሪካውያን መራጮችም ኢኮኖሚውን ሊያስተካክል የሚችል ለውጥ መራባቸውን ሲገልፁ ተደምጧል።
ጋሉፕ ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አሜሪካ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘች ነው ብለው የሚያምኑት 25 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አመላክቷል።
62 ከመቶ አሜሪካውያን የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ አምርቷል ብለው ማመናቸውም መራጮች ለውጥን በመሻት ፊታቸውን ወደ ትሬምፕ እንዲያዞሩ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል።
2. በመጥፎ ዜናዎች አለመሸበራቸው
ትራምፕ የ2020ውን የምርጫ ውጤት አልቀበልም ብለው በጥር ወር 2021 በካፒቶል አዳራሽ ነውጥ ከመፍጠራቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ክሶች ቢቀርቡባቸው ሳይረበሹ ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ለምርጫው ደርሰዋል።
ምርጫው ሲቃረብ ተደራራቢ ክሶች መቅረባቸውም የፓርቲያቸው ሪፐብሊካን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ለዘብተኛ አሜሪካውያንም ትራምፕ የሚያነሱት "የፖለቲካዊ ሻጥር ሰለባ ነኝ" ቅሬታን ቆም ብለው እንዲመለከቱት ማድረጉ ነው የሚነገረው።
ከወሲብ ቅሌትና ከምርጫ የማጭበርበር ሙከራ ጋር የተያያዙ በርካታ ክሶች እየቀረቡባቸው እንኳን የትራምፕ የድጋፍ ምጣኔ ከ40 በመቶ አልወረደም።
3. በህገወጥ ስደተኞች ላይ መዛታቸው
በአሜሪካ ምርጫ ከኢኮኖሚ ባሻገር የመራጮችን ስሜት ሰቅዞ የሚይዝ ጉዳይ መዝዞ መቅረብ ለድል ያበቃል።
ዴሞክራቶች የጽንስ ማቋረጥ (ውርጃ) ካርድን ሲመዙ፥ ትራምፕ የአሜሪካ ፈተና ናቸው እያሉ በስድብ የሚወርፏቸውን ህገወጥ ስደተኞች ከሀገር አባርራለሁ የሚለውን ዛቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።
በባይደን የስልጣን ዘመን የአሜሪካ ድንበርን አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶችም መራጮች ህገወጥ ስደትን ለማስቆም ከዴሞክራቶች ይልቅ ትራምፕ ላይ መተማመን እንዳላቸው አሳይተዋል።
4. አሜሪካ ለዘነጋቻችሁ መጣሁላችሁ ማለታቸው
ትራምፕ አሜሪካ ረስታናለች፤ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተዘንግተናል ብለው ለሚያምኑ ወገኖች የተለየ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የፈጠሩ ኢንዱስትሪዎች ቀረጥ እቀንሳለሁ ማለታቸውም ይታወሳል። ይህም ለዴሞክራቶች ድምጻቸውን ሲሰጡ የነበሩ የሰራተኞች ማህበራትን ወደ ፓርቲያቸው መሳብ ችሏል።
5. ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ጠንካራ ሆነው መታየታቸው
የትራምፕ ተቺዎች የ78 አመቱ አዛውንት ከአምባገነን መሪዎች ጋር ያመሳስሏቸዋል፤ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ አጋሮችም አሳጥተዋል ይላሉ።
አወዛጋቢው ትራምፕ ግን አይገመቴነታቸውን እንደ ጥንካሬ ይመለከቱታል፤ በዋይትሃውስ ቆይታቸው አሁን የሚታዩት ጦርነቶች አለመጀመራቸውንም ያነሳሉ።
በርካታ አሜሪካውያን ሀገራቸው በዩክሬን እና ጋዛ የሚካሄዱ ጦርነቶችን ለመደገፍ ቢሊየን ዶላሮችን መላኳን አይደግፉትም።
እናም ትራምፕ ከሃሪስ የተሻለ ጦርነቶቹን የሚያስቆም ጠንካራ አቅም አላቸው ብለው የሚያምኑት ይመርጧቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሃሪስ ሊያሸንፉ ይችላሉ ምክንያቱም፦
1. ትራምፕን ስላልሆኑ
ዶናልድ ትራምፕ በ2020ው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በባይደን በ7 ሚሊየን መራጮች ተበልጠው በምርጫው ይሸነፉ እንጂ በርካታ ደጋፊ ነበራቸው።
በዚህኛው ምርጫ ሃሪስ “ፋሺስት” እያሉ የሚጠሯቸው ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ የአሜሪካ ዴሞክራሲ አፈር በላው እያሉ ፍርሃት መልቀቅን መርጠዋል። ትራምፕ ዳግም ዋይትሃውስ ከዘለቁ አሜሪካ ወደማያቋርጥ“ድራማ ወደ ግጭት” ትገባለችም ብለዋል።
ሬውተርስ ከኢፕሶስ ጋር ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ከአምስት አሜሪካውያን አራቱ ሀገሪቱ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣች መሆኑን ያምናሉ። በዚህ ሁኔታ የትራምፕ ዳግም መመረጥ የቁልቁለት ጉዞውን ያፋጥናል ብለው የሚያምኑ ለዘብተኛ ሪፐብሊካኖች እና ገለልተኛ መራጮች ሃሪስን ሊመርጡ ይችላሉ።
2. ባይደንን ስላልሆኑ
ጆ ባይደን ከምርጫው ፉክክር ራሳቸውን እስኪያገሉ ድረስ ዴሞክራቶች በምርጫው መሸነፋቸው አይቀሬ መሆኑ ለእርግጠኝነት ቀርቦ ነበር። ፓርቲው ሃሪስን እጩ ተፎካካሪ አድርጎ ከመረጠ በኋላ ግን ትራምፕን ለማሸነፍ በአንድነት ሰርቷል።
ሪፐብሊካኖች ሃሪስን ከባይደን ድጋፍ ካላገኙ ፖሊሲዎች ጋር እያያዙ ሊነቅፏቸው ቢሞክሩም ሃሪስ ከባይደን በተለያዩ ጉዳዮች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። እድሜያቸው (60) ከባይደንም ሆነ ከትራምፕ አንጻር በነጩ ቤተመንግስት አሜሪካን ለማገልገል የተሻለ መሆኑንም አሳይተዋል። መራጮች ከባይደን የእድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ሲያነሷቸው የነበሩ ቅሬታዎች በሃሪስ ተፈቷል።
3. የሴቶች መብት ተቆርቋሪ ሆነው መቅረባቸው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ጽንስ ማቋረጥ ህገመንግስታዊ መብት እንዲሆን ውሳኔ ባሳለፈበት አመት የሚካሄደው ምርጫ ለሃሪስ ድል ትልቁን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በ2022ቱ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ጉዳዩ ዴሞክራቶች እንዲመረጡ ማድረጉ ይታወሳል።
በዘንድሮው ምርጫ 10 ግዛቶች መራጮች የጽንስ ማቋረጥ እንዴት ይፈጸም በሚለው ጉዳይ ከምርጫው ጎን ለጎን ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ ጠይቀዋል። ይህም ካማላ ሃሪስን የሚደግፉ መራጮች በነቂስ ድምጽ እንዲሰጡ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ሃሪስ የአሜሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያደርጉት ፉክክር በራሱ በርካታ ሴት መራጮችን ሊያስገኝላቸው ይችላል።
4. የኮሌጅ ተማሪዎችና አዛውንቶች ላይ ማተኮራቸው
ሃሪስ በምርጫ ቅስቀሳቸው የኮሌጅ ምሩቃን እና አዛውንቶች ላይ ትኩረት አድርገዋል። ይህም ወጣት ወንዶች እና የኮሌጅ ዲግሪ የሌላቸው ሰዎች ላይ ካተኮሩት በተሻለ ለምርጫ ዋጋ የሚሰጡ ሰዎችን እንደሚያስገኝላቸው ተጠብቋል።
5. ለምርጫ ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰብና በመጠቀማቸው
የአሜሪካ ምርጫ ውድ መሆኑ ይታወቃል። የሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 997.2 ሚሊየን ዶላር ሰብስቧል። ይህም ትራምፕ ከሰበሰቡት (338 ሚሊየን ዶላር) በሶስት እጥፍ ገደማ ይበልጣል።
በሀምሌ ወር ባይደንን የተኩት ካማላ ሃሪስ ከጥር 2023 ጀምሮ የምርጫ ቅስቀሳ ከጀመሩት ትራምፕ የተሻለ ገንዘብ መሰብሰብ ችለዋል። ለምርጫ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ለማስታወቂያ ውሏል።
ማስታወቂያ ላይ የሃሪስ ቡድን ያከናወነው ስራ የምርጫውን ውጤት በሚወስኑ ሰባቱ ግዛቶች በሚታየው ትንቅንቅ ውስጥ የራሱን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።