አደጋውን አጥፍቶ ጠፊዎች አቀናብረውታል የተባለ ሲሆን አንዱ ራሱን መግደሉ ተገልጿል
በቱርክ መዲና አንካራ የሽብር አደጋ መድረሱ ተገለጸ።
የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚንስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ዛሬ እሁድ ረፋድ ሁለት የሽብር አደጋዎች ተፈጽመዋል።
አደጋውን ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች በተሽከርካሪ ከመጡ በኋላ የቱርክ ብሔራዊ የደህንነት ዋና ማዘዣን ኢላማ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
አንዱ አጥፍቶ ጠፊ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት እርምጃ እንደተወሰደበት ሲገለጽ ሁለተኛው አጥፍቶ ጠፊ ደግሞ በራሱ ላይ ያጠመደው ቦምብ ፈንድቶ ሁለት ፖሊሶች ላይ ቀላል ጉዳት ማድረሱን አናዶሉ ዘግቧል።
የሽብር አደጋውን ተከትሎም ቱርክ በመላ ሀገሪቱ ጠንካራ የጸጥታ እና የደህንነት ስምሪት መስጠቷ ተገልጿል።
የአንካራ ፖሊስም ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ አደጋው የደረሰበት አካባቢ ለሚዲያ እና ኮሙንኬሽን ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።
የቱርክ ህግ አውጪ ምክር ቤት ከሶስት ወራት እረፍት በኋላ ዛሬ ከሰዓት እንደሚከፈት ይጠበቃል።