የቴስላ ሳይበርትራክ መኪና ላስ ቬጋስ በሚገኘው የትራምፕ ሆቴል ፊት ለፊት መፈንዳቱ ተነገረ
የቴስላ ሳይበርትራክ መኪና ከመፈንዳቱ በፊት በነዳጅ እና በርችት የተሞላ ነበር ተብሏል
በፍንዳታው የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 7 ሰዎች ቆስለዋል
በአሜሪካዋ ላስቬጋስ በሚገኘው የትራምፕ ሆቴል ፊት ለፊት የቴስላ ሳይበርትራክ መኪና መፈንዳቱ ተነግሯል።
በነዳጅ እና ርችት ተሞልቶ ነበር የተባለው ሳይበርትራክ መኪና ላስቬጋስ፣ ኔቫዳ በሚገኘው የዶናልድ ትራምፕ ሆቴል መግቢያ በር ላይ መፈንዳቱ ተገልጿል።
በፍንዳታው የመኪናው አሽከርካሪ ወዲያው ህይወቱ ሲያልፍ ሌሎች 7 ሰዎች መቁሰላቸውም ነው የተነገረው።
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ፤ መኪናው ላይ በርካታ የነዳጅ መያዣዎች እና ርችት ተጭነው ነበር ብሏል።
የአሜሪካ የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ድርጊቱ የሽብር ተግባር ሊሆን ይችላል ወይ የሚለውን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
የትራምፕ ሆቴል የሳይበርትራክ ፍንዳታ አንድ ግለሰብ የአይኤስ ባንዲራ በያዘ መኪና በኒው ኦርሊየንስ በርካታ ሰዎችን በመግጨት ቢያንስ 15 ሰዎችን ከገደለ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የተከሰተ ነው።
ይህንን ተከትሎም ሁለቱ ጥቃቶች ዙሪያ ግንኙነት ስለመኖሩ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ነው ኤፍቢአይ ያስታወቀው።
በተጨማሪም ፍንዳታው የሆቴሉ ባለቤት ከሆኑት ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወይም የቴስላ ባለቤት ከሆነው ኢላን መስክ ጋር የተያያዘ ሊሆን ስለመቻሉም እየመረመረ መሆኑንም አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ መርማሪዎች በላስ ቬጋስ ከትራምፕ ሆቴል በር ላይ ከቴስላ ተሽከርካሪ ቃጠሎ ከኒው ኦርሊያንሱ ጥቃት ጋር ግንኙነት ሊኖር ወይም አለመኖሩን እየመረመሩ ነው ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ሁለቱን ክስተቶች የሚያገናኝ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ሲል ባይደን ተናግረዋል።