ቴስላ ኩባንያ በቅርቡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መኪኖችን መጥራቱ ይታወሳል
ቴስላ ኩባንያ 700 ሺህ የተሸጡ መኪኖችን እንደሚሰበስብ ገለጸ።
በዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ በሆነው ኢለን መስክ የተመሰረተው ቴስላ ኩባንያ ለ700 ሺህ መኪኖች ጥሪ አቅርቧል።
መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው ይህ ኩባንያ ሳይበር ትራክ እና ሞዴል ዋይ የተሰኙ መኪና ሞዴሎች ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ኩባንያው አሁን ጥሪ ላደረገላቸው መኪኖች ነጻ የቴክኒክ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቋል።
በተለይም ሳይበር ትራክ በመባል የሚታወቀው የመኪና ሞዴል ችግር አለበት በሚል ከገበያ ላይ እንዲሰበሰብ ጥሪ ሲደረግ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ቴስላ ኩባንያ ባለፈው የካቲት ወር ላይ ለ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን መኪኖች ጥሪ አቅርቦ ነበር።
እንዲሁም ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ደግሞ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያህል መኪኖች የመጋጨት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል በሚል ጥሪ አቅርቦ ተገቢውን ጥገና መስጠቱም አይዘነጋም።
የመኪና አምራች ኩባንያዎች ለደንበኞቻቸው የተሸጡ መሰል የቴክኒክ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጥሪ ማድረግ የተለመደ ሲሆን ጥገናዎችን በነጻ ይሰጣሉ።
ኢለን መስክ ሹፌር አልባ መኪኖችን በማምረት ለዓለም ገበያዎች በማቅረብ ላይ ሲሆን አሜሪካ እና አውሮፓ ደግሞ ዋነኛ መዳረሻዎች ናቸው።
ከቻይና ብርቱ ፉክክር የገጠመው ቴስላ ኩባንያ በተለይም እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት በቢዋይዲ ኩባንያ ተበልጧል።