በታይላንድ ሙሽራው በሰርጉ ላይ ሙሽሪንትን ጨምሮ አራት ሰዎችን ገደለ
ሙሸራው፣ ሙሽሪትን፣ እናቷን እና እህቷን በስርግ ስነ ስርዓት ላይ ተኩሶ መግደሉ ተነግሯል

በስፍራው የነበሩ ሰዎች ጥንዶቹ በሰርጉ ላይ እያሉ ስጨቃጨቁ ነበር ብለዋል
በታይላንድ አንድ ሙሽራ በሰርጉ እለት ሙሽሪትን ጨምሮ አራት ሰዎችን ተኩሶ መግደሉን ፖሊስ አስታውቋል።
የቀድሞ ወታር እና የፓራ አትሌት የነበረው ሙሽራው፣ ባለቤቱን ጨምሮ አራት ሰዎችን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ራሱን ማጥፋቱንም ፖሊስ ገልጿል።
የ29 ዓመቱ ቻቱሮንግ ሱክሱክ እና የ44 ዓመቷ ካንቻና ፓቹንቱክ በሰሜን ምሥራቅ ታይላንድ ባሳለፍነው ቅዳሜ ነበር የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን የፈጸሙት።
በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ የነበሩ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት ሙሽራው የሰርግ ስነ ስርዓቱን አቋርጦ ከወጣ በኋላ የጦር መሰሪያ ይዞ ተመልሶ ነው ጥቃቱን የሰነዘረው።
በዚህም የ44 ዓመቷ ሙሽሪት ካንቻና ፓቹንቱክ ጨምሮ፣ የ62 ዓመት እድሜ ያላቸው የሙሽሪት እና የ38 ዓመት እድሜ ያላት የሙሽሪት እህትን ተኩሶ መግደሉን አስታውቀዋል።
በዚሁ ወቅት በተባራሪ ጥይት ሁለት የሰርጉ ታዳሚዎች መመታታቸውን እና ወደ ሆስፒታል ከተወደሱ በኋላ የአንዱ ህይወት ማለፉንም ተዘግቧል።
ሙሽራው ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ የራሱን ህይወት ማጥፋቱም ነው የተነገረው።
ፖሊስ ሙሽራው ቻቱሮንግ ሱክሱክ "በወቅቱ በጣም ሰክሮ ነበር" ያለ ሲሆን፤ ግድያውን የፈጸመበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም ብሏል።
በስርጉ ላይ የታደሙ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ የታይላድ መገናኛ ብዙሃን ባወጡት መረጃ፤ ሙሽሮቹ በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ ሲጨቃጨቁ ነበር ብለዋል።
ሙሽራው ቻቱሮንግ በእሱ እና በሚስቱ ካንቻና መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት ምቾት ይነሳው እንደነበረም ተዘግቧል።
ሆኖም ግን ፖሊስ “እነዚህ ጥርጣሬዎች ናቸው” ያለ ሲሆን፤ መረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን እና በቅርቡ ምክንያቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የ29 ዓመቱ ቻቱሮንግ ሱክሱክ እና የ44 ዓመቷ ካንቻና ፓቹንቱክ ጋብቻ ከመፈጸማቸው በፊት ለ3 ዓመታት በጋራ መኖራቸውን የታይላንድ ሚዲያዎች ዘግበዋል።