10ኛው የግንኙነቱ ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
10ኛው የአፍሪካ-አውሮፓ ህብረት ጉባዔ ታካሄደ
የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ተቋማዊ የግንኙነት ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ ለ10ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ጉባዔ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን የተመራ ልዑክ ተሳትፏል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች አያያዝና በህግ ስርዓት መከበር ላይ በአፍሪካ መሻሻሎች መታየት መጀመራቸውን በጉባዔው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የገለጹት ሙሳ ፋኪ ሰላምና ፀጥታን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኮሚሽኑ ጋር የመስራት ዝግጁነትና ፍላጎት በህብረቱ ዘንድ አለ ብለዋል፡፡
በአህጉሪቱ ምጣኔሃብታዊ መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል ያሉም ሲሆን ሽብርተኝነት፣የድንበር ዘለል ወንጀሎች መበራከት እና አክራሪነት እንዲሁም መጤ ጠልነት የአህጉሪቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ህብረቱ በሊቢያ ጉዳይ በማድረግ ላይ ያለው ድጋፍ ትልቅ መሆኑን ገልጸው ችግሩ የቀጣናው ጭምር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠርና አንድ የጋራ ገበያን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ህብረቱ መደገፉም በተቋማቱ አባል ሃገራትና ከአጋሮቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
ኡርሱላ በህብረቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተካተቱበትን ልዑክ ይዘው የተገኙት፡፡ ይህ በተቋማዊ ግንኙነቱ ታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅና ለግንኙነቱ መጠናከር ኮሚሽኑ ያለውን ፍላጎት እንደሚያሳይም ገልጸዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታ፣ስራ ዕድል ፈጠራ፣ አየር ንብረት እና ምጣኔ ሃብትን ጨምሮ በሰዎች ዝውውር፣በቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም በጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚወያዩም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ረገድ ተቋማቱ ብዙ ኃላፊነት አለባቸው ያሉ ሲሆን የፀጥታ እና ደህንነት ስራዎቹ ህብረቱ የጥይት ድምፅ የማይሰማባትና ለልማት የተመቸች አፍሪካን ለመፍጠር የያዘውን ራዕይ ለመደገፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ ያለውን “ርሃብ” ለማስታገስ እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡
ለዚህም ባለፉት 10 ዓመታት ከገኘነው ልምድና ተሞክሮ ተምረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ከጉባዔው መልስ ጋዜጣሚ መግለጫው በሚመለከታቸው የህብረቱና የኮሚሽኑ ባለስልጣናት ተሰጥቷል፡፡
የህብረቱ የጸጥታና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር እስማዔል ቼርጊ በጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ይበልጥ ቅድሚያ ሰጥተን ተቀራርበን እንደምንሰራ አልሸባብን ለመዋጋት በአሚሶም የሚደረጉ ጥረቶች እና በሳህል አካባቢ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የዛሬው ውሏችን ይህንና ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት ይበልጥ ለማጠናከር የምንችልበትን አጋጣሚ የፈጥረ ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የጋራ ደህንነት ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው ኢንቨስትመንት እና ስራ ፈጠራ መረጋጋትን በእጅጉ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
ሳንረጋጋ ልናድግ፣ኢንቨስት ልናደርግና ስራንም ልንፈጥር አንችልም ያሉም ሲሆን የአፍሪካ ችግር የአውሮፓ የአውሮፓም የአውሮፓ እንደሆነ፣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግና ይህንን እንደሚያግዙ እንዲሁም ከሳይበር ደህንነትና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የተቋማዊ ግንኙነቱ አጀማመር
ለ10ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ግንኙነቱን የተመለከተ ፓለቲካዊ አመራር የሚሰጥበት ነው። በየአመቱ የሚካሄድም ሲሆን ባለፈው አመት በቤልጂየም በብራሰልስ ተካሂዷል፡፡ ግንኙነቱ እ.ኤ.አ በ2000 በካይሮ ከተጀመረ በኋላም በየአመቱ እድገትን እያሳየ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 በወጣው ስትራቴጂም ይመራል፡፡
በመሪዎች ደረጃ በየሶስት አመቱ የሚካሄድ ግንኙነቱን የተመለከተ ጉባኤም አለ፡፡ ጉባዔው ግንኙነቱ እንዴት መቃኘትና ለየትኞቹ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ፖለቲካዊ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ነው፡፡
በስተመጨረሻም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል የሚውል የ10 ሚሊዬን ዩሮ ድጋፍ አድርጎ ጉባዔው ተጠናቋል፡፡