በትግራይ ክልል የህግ የበላይነት በፍጥነት እንዲረጋገጥ የተመድ ዋና ጸኃፊ ጥሪ አቀረቡ
የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል
ዋና ጸኃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተነጋግረዋል
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸውን የዋና ፀኃፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ጁዣሪች ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ፣ ጉተሬዝ የህግ የበላይነትን በፍጥነት ማስፈን ፣ ለሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ ማድረግ ፣ ማህበራዊ ትስስርን ማስፈን ፣ ሁሉን አቀፍ እርቅ መፈጸም እንዲሁም የህዝብ አገልግሎቶችን አቅርቦት እንደገና መጀመር እና ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ህብረትን ተነሳሽነት ለመደገፍ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኑንም ነው ዋና ጸኃፊው የገለጹት፡፡ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸውም የገለጹ ሲሆን ድርጅቱ ለስደተኞች ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች እና በችግር ላይ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተጨማሪ ከተባበሩት መንግስታት ተወካዮች እና ከቀጣናዊ ድርጅት መሪዎች ጋር ባደረጓቸው በርካታ ውይይቶችም ከላይ የተጠቀሱትን መልዕክቶች ማስተላለፋቸውም ተጠቁሟል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ኃይል ጥቃት መፈጸሙ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መቀሌን መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡ ሠራዊቱ መቐሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሠራዊቱ ንብረት የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ የሕወሓት የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠሩን ገልጿል፡፡
የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻው መጠናቀቁን የገለጸው የፌዴራል መንግሥት በቀጣይነት በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን እና ከመከላከያ ሠራዊት የከዱ አመራሮችን የማደን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በወንጀል የሚፈለጉ አመራሮች ይገኙበታል የተባለው ስፍራ በመከላከያ ሠራዊት ተከቦ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የፌዴራል መንግሥትን እና ሕወሓትን ለማሸማገል ቢሞክሩም ከወንጀለኞች ጋር ለድርድር አልቀመጥም ያለው የፌዴራል መንግሥት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡