የሱዳን የሽግግር መንግስትና ዋነኛው ተቃዋሚ የተፈራረሙት ስምምነት በብዙ ሱዳናውያን ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ
ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ ሱዳን ከእስላማዊ መንግስት እንድትላቀቅ የሚያደርጋት ነው
የሱዳን የሽግግር አስተዳደር እና ተቃዋሚው በሀገሪቱ ከኃይማኖት ነጻ የሆነ መንግስት እንዲመሰረት ተስማምተዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌፍተናንት አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የሱዳን ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ - ሰሜን (SPLM-N) ሊቀመንበር ኮማንደር አብዱላዚዝ አል-ሂሉ ፣ በሱዳን ከኃይማኖት የተፋታ ነጻ መንግስት እንዲመሰረት ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተስማምተዋል፡፡
ሁለቱ አካላት 6 ነጥቦች ያሉት የመርሆዎች መግለጫም ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልፋ ኪር እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዴቪድ ቢዝሌይ በተገኙበት ፣ በጁባ ተፈራርመዋል፡፡
የሀገሪቱን አንድነት ፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ኃይማኖት እና መንግስት መለያየት እንዳለበት በስምምነቱ መርሆች ውስጥ ተካቷል፡፡ ሱዳን በርካታ ብሔሮች ፣ የተለያዩ ኃይማኖቶች እና ባህሎች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ እነዚህ ልዩነቶች እውቅና አግኝተው ፣ በሕገ-መንግስት መካተት እንዳለባቸው እና እኩል ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ስምምነቱ ይደነግጋል፡፡ ይህ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሱዳን ከእስላማዊ መንግስት እንድትላቀቅ የሚያደርጋት ነው፡፡
በሽግግር አስተዳደሩ እና በዋነኛ ተቃዋሚው (የሱዳን ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ) መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት ታዲያ በብዙ ሱዳናውያን ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ የሀገሪቱ እስላማዊ የኃይማኖት ተቋማት እና የኃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በርካታ ሱዳናውያን ስምምነቱን ተቃውመዋል፡፡ ስምምነቱን ወደ ተግባር የመለወጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጣ ሊቀሰቀስ እንደሚችል እና ህዝቡ ለተቃውሞ ጎዳና ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ከ90 እስከ 97 በመቶ የሚሆነው የሱዳን ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው፡፡