አል-ማክቱም ፋውንዴሽን በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ ቀጥሏል
በአዲስ አበባ 2 ት/ቤቶችን የገነባው ፋውንዴሽኑ ለመምህራን ስልጠና መስጠትም ጀምሯል
ኮሮና ክፉኛ የተፈታተነውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ በቀጣይነት ለመደገፍ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን መንደፉን ፋውንዴሽኑ ገልጿል
አል-ማክቱም ፋውንዴሽን በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ ቀጥሏል
በኮሮና ምክንያት የተቋረጠው የመማር ማስተማር ስራ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በአብዛኛው ተጀምሯል፡፡
የቫይረሱ መከሰት ያስተጓጎለውን የትምህርት ጌዜ ለማካካስ እና አሁንም ስርጭቱን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚፈጥሩትን ተጽዕና ለመቋቋም መንግስት የተለያዩ አካላትን ድጋፍ ይሻል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንን ጫና ለመቀነስ እኔም አስተምራለሁ በሚል ንቅናቄ ንቅናቄ ጡረታ የወጡትን ጨምሮ የመምህርነት ክህሎት ያላቸው ሰዎች ሥራውን እንዲያግዙ ያቀረበው ጥሪ አንዱ ድጋፍ የሚፈለግበት ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በመማሪያ ክፍሎች ማነስ የተማሪዎችን መጨናነቅ ለመቀነስ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እንዲሁም ት/ቤቶችን መገንባት እና ቁሳቁሶችን ማሟላትም የተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ድጋፍ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውጭ ሀገራት ፋውንዴሽኖች አንዱ የሆነው አል-ማክቱም ፋውንዴሽን በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቶ የትምህርት ቤቶችን መምህራን ደሞዝ እና ሌሎች ወጪዎችንም በመሸፈን ላይ የሚገኘው ፋውንዴሽኑ የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ ሌሎች ተግባራትንም በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የአል-ማክቱም ፋውንዴሽን የቦርድ አባል በፋውንዴሽኑ በየካ ክ/ከተማ የተገነባው ት/ቤት ሲመረቅ
ሌሎች ትምህርት ቤቶችን እና ኮሌጅም ለመገንባት ፋውንዴሽኑ ከመንግስት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የገንዘብ ሚኒስትር ሼክ ሀምዳን ቢን ራሺድ አል-ማክቱም ስር የሚገኘው ፋውንዴሽኑ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 13 ትምህርት ጽ/ቤት ጋር የቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ የሚችልበትን የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ለማሰልጠንም እየሰራ ነው፡፡ ስልጠናውን ለመስጠት 30 የተመረጡ የትምህርቱ ዘርፍ ባለሙያዎችን ሱዳን ካርቱም ልኮ የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
በየካ ክ/ከ የወረዳ 13 ም/ሥራ አስፈጻሚ እና የት/ጽ/ቤ ኃላፊ ምህረት አርጋጎ እና የአል-ማክቱም ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሲፈራረሙ
የአል-ማክቱም ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አብዱሰላም አደም ኮኮ ለአል ዐይን ኒውስ እንደገለጹት ሱዳን ሰልጥነው የመጡት ባለሙያዎች በኮሮና ምክንያት ለመምህራን የሚሰጡት ስልጠና ለወራት የተራዘመ ቢሆንም አሁን ላይ ስልጠናውን ለማስጀመር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡
አብዱሰላም አደም ኮኮ -የአል-ማክቱም ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር
ስልጠናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ፋውንዴሽኑ ካስገነባቸው ት/ቤቶች አንዱ የሚገኝበት የየካ ክፍለ ከተማ ት/ጽ ቤት ኃላፊ አብዮት ድንቁ ተናግረዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በአዲስ አበባ ለሚገኙ በርካታ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የስልጠና እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
አብዮት ድንቁ -የየካ ክ/ከ ት/ጽ/ቤት ኃላፊ
አል-ማክቱም ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኤምሬቶች ጋር በመሆን በተያዘው ዓመት ውስጥ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ለማከናወን ያቀደ ሲሆን ከፕሮጄክቶቹ መካከል በ50 ት/ቤቶች መካከል የሥርዓተ-ትምህርት (የካሪኩለም) ውድድር ማድረግ ይገኝበታል የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እንደገለጹት፡፡
በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ 10 ት/ቤቶችን በመምረጥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ካሪኩለሙ እንዲተገበርባቸው ይደረጋልም ብለዋል፡፡ ለተወሰኑ መምህራን የማስተርስ እና የፒኤችዲ የትምህርት ዕድል እንደሚመቻችም አብዱሰላም አደም ኮኮ ተናግረዋል፡፡
አል-ማክቱም የሚያከናውነው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ረገድ ችግሮች በሚስተዋሉባት ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጨማሪ ፈተና ሆኗል፡፡ ይን ፈተና ለመቋቋም መሰል በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሚያደርጉት ድጋፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡