የኤርትራው ፕሬዝደንት ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር መልዕክት ላኩ
ደብዳቤው የተላከው የሱዳን ባለስልጣን “የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር ድንበር ላይ እንደሚገኙ መረጃ አለን” ማለታቸውን ተከትሎ ነው
በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር ያለው ውጥረት በሰላም እንዲፈታ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጠይቀዋል
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ የተላከ የጽሁፍ መልዕክት ተቀብለዋል፡፡
የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ እና የፕሬዝደንት ኢሳያስ አማካሪ የማነ ገበረ አብ ናቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ መልዕክቱን ያደረሱበት፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት በመልዕክታቸው ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር ባለው ሁኔታ ስጋታቸውን በመግለፅ ሀገራቸው ከድንበር ውጥረቱ ጋር ምንም የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
የቀጣናውን ሰላም ፣ መረጋጋት እና ደህንነት በሚያረጋግጥ መንገድ ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ውጥረት በሰላም እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኤርትራ እና በሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እና ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ፕሬዝደንት ኢሳያስ ያነሱት፡፡
በትናንትናው እለት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አባል የሆኑት ያሲር አል አታ ከአል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ “የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ መከላከያን መለዮ ለብሰው አብረው ድንበር ላይ እንደሚገኙ መረጃ አለን” ማለታቸውን ተከትሎ ነው ፣ የኤርትራው ፕሬዝደንት ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር መልዕክቱን የላኩት፡፡