ፍርድ ቤት በአቶ ልደቱ ላይ የተከፈተውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ቢዘጋም አቶ ልደቱ ከእስር አልተለቀቁም
ኢዴፓ መንግስትን ለመክሰስ መዘጋጀቱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ገለጹ
በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ፖሊስ ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ ማጠናቀቁን ዛሬ ለቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት ገልፆ አቃቤ ህግ ክስ እስኪመሰርት ድረስ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን አልተቀበለም፡፡
ይህን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ፍርድ ቤቱ የእስካሁኑን የምርመራ መዝገብ መዝጋቱን ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
የፖሊስን የምርመራ መዝገብ የዘጋው ፍርድ ቤቱ አቶ ልደቱ አያሌው በሌላ መዝገብ የዋስትና ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ልደቱ በሁለት ጠበቆቻቸው አማካኝነት ላነሷቸው ጥያቄዎች ፍርድ ቤቱ በቂ ምላሽ እንዳልሰጣቸው የገለጹት አቶ አዳነ መዝገቡ ከተዘጋ በኋላ ፍርድ ቤቱ በነጻ ሊያሰናብታቸው ሲገባ ፖሊስ ወደ ማረፊያ ጣቢያ እንደወሰዳቸው ነው የተናገሩት፡፡
አንድ እስረኛ በሕጉ መሰረት በማረፊያ የሚቆየው በቁጥጥር ስር ዉሎ ፍርድ ቤት እስኪቀርብ ለ 48 ሰዓታት ፣ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠር ሲሰጠው አሊያም ዋስትና እስኪያቀርብ መሆኑን ያነሱት አቶ አዳነ ይሁንና የተከሰሱበት ጉዳይ እንደማያስጠይቃቸው በይኖ ቀጠሮ ባልሰጠበት ሁኔታ ወዲያው መለቀቅ እንደነበረባቸው አንስተዋል፡፡ “ዋስትናም ካስፈለገ ዛሬ ማቅረብ ቢችሉም ነገ በአዲስ መዝገብ እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል” ነው ያሉት አቶ አዳነ፡፡
በመሆኑም ኢዴፓ ከጠበቀቹ ጋር በመሆን በነገው እለት ሁለት መዝገብ ለመክፈት ማቀዱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ከአል ዐይን ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አንደኛው መዝገብ በፍርድ ቤቱ የታዘዘውን የዋስትና ጥያቄ የሚቀርብበት ሲሆን ሌላኛው የመንግስት አቃቤ ህጎች ላይ ክስ የሚመሰረትበት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
የዋስትና ጥያቄውን ተቀብሎ ፖሊስ ሊለቃቸው ይችላል ወይ በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ አዳነ ሲመልሱ “እስካሁን ካለው ተሞክሮ አንጻር ጥርጣሬ አለን” ብለዋል፡፡ “በመንግስት ላይ ክስ ለመመስረት የምንከፍተው መዝገብ አንደኛው ምክንያትም ፖሊስ የፍርድ ቤት ዉሳኔን መተግበር አለመቻሉን በመቃወም ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ለተጠረጠሩበት ክስ ማስረጃ ሳይገኝ እና ለሚያነሱት ጥያቄ አሳማኝ እና በቂ ምላሽ ሳይሰጣቸው እስካሁን ያለአግባብ መታሰራቸው እንዳለ ሆኖ ፖሊስ ሊያሰናብታቸው ሲገባ ወደ ጣቢያ ወስዷቸዋል” ያሉት አዳነ “በነገው እለት የዋስትና ጥያቄ ሲቀርብ ፣ ፖሊስ ሌላ ክስ መስርቶ ለተጨማሪ ጊዜ እንዳያቆያቸው ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው “ቢሾፍቱ ከተማ ላይ የተቀሰቀሰውን ቀውስ አስተባብረሃል ፤ በገንዘብም በመደገፍ ተጠርጥረሃል” ተብለው ከአምስት ሳምንታት በፊት ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡