የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ዋና ከተማ በአማጺያን መከበቧ ተገለጸ
አማጺያን ኃይሎች በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ሁለት ሦስተኛ ክፍል መቆጣጠራቸው ይነገራል
በሀገሪቱ ዋና ከተማ ባንጉይ ያለው ሁኔታ “የምፅዓትጊዜ ይመስላል” ሲሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ገልጸዋል
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ዋና ከተማ ባንጉይ ያለው ሁኔታ “የምፅዓትጊዜ ይመስላል” ሲሉ የሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማርቲን ዚጌሌ በየቀኑ በመላ ሀገሪቱ ውጊያዎች እንደሚካሄዱና ከባንጉይ ያለ ታጣቂ አጃቢ መውጣት እንደማይችሉ ገልጸዋል ፡፡
የተባበሩት መንግስታት በማዕከላዊ አፍሪካ ባለፈው ወር ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ 200 ሺህ በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው መሰደዳቸውን አስታውቋል፡፡ ከነዚህም 92 ሺህ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሀገር ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ የተሰደዱ ሲሆን ከ 13 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ካሜሮን ገብተዋል፡፡
የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ስደተኞች ካምፕ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ
አማጺያን ኃይሎች በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ሁለት ሦስተኛ ክፍል መቆጣጠራቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ምንም እንኳን እንደ አልማዝ እና ዩራኒየም ባሉ ሀብቶች የበለፀገች ቢሆንም ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ከአፍሪካ በጣም ደሃ እና ያልተረጋጋ ሀገራት አንዷ ነች፡፡ የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ግማሽ ያህሉ የሀገሪቱ ህዝብ በሰብአዊ እርዳታ ላይ ጥገኛ ነው ፡፡
በባንጉይ ዙሪያ ያሉ አማፅያን ኃይሎች በታህሳስ ወር በተካሔደው ምርጫ ፕሬዚዳንት ፋስታ አኮዥ ቱዴሀ ዳግም መመረጣቸውን ትክክለኛነት ባለመቀበላቸው ከስልጣን እንዲወገዱ ይፈልጋሉ ፡፡
ከተማዋ በተባበሩት መንግስታት ፣ በሩሲያ እና በሩዋንዳ ወታደሮች በሚደገፉ የመንግስት ኃይሎች እየተጠበቀች ትገኛለች ፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጇል፡፡
በምርጫው ሦስተኛ ደረጃን የያዙት ሚስተር ዚጌሌ ፣ የሁሉም ሰው ትኩረት በባንጉይ እና በምስራቅ ካሜሩን መካከል ያለው ዋና የአቅርቦት መስመር እንዳይዘጋ መከላከል ነው ብለዋል፡፡
“ከፍተኛ የታጠቀ ጦር ካለጀበኝ በስተቀር ከባንጉይ መውጣት አልችልም” ያሉት ሚስተር ዚጌሌ አክለውም “ሕዝቡን አስቡት ፣ ከስጋት በተጨማሪ እገዳዎች እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታይ በእውነቱ የምፅዓት ቀን ነው” ሚመስለው ብለዋል፡፡
ቢያንስ 12 ሺህ ሰላም አስከባሪዎች በሀገሪቱ የሚገኙ ሲሆን ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎች እንዲሰማሩ የተባበሩት መንግስታት ሀሳብ አቅርቧል፡፡