“ኤች.አር 6600 የተመለሱ ጥያቄዎችን ነው የሚያነሳው”- አምባሳደር ዲና
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ፎረም ውጭ መሆኗ ተገቢ አለመሆኑን በሙኒክ መድረክ ማስረዳቷንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት
አምባሳደር ዲና የብራሰልስ እና የሙኒክ መድረኮች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማራመድ የተቻለባቸው ነበሩም ብለዋል
ኤች.አር 6600 የሚያነሳቸው ጥያቄዎች መጀመርያውኑ የተመለሱ ናቸው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ማዕቀብ ይዳርጋል በተባለው ኤች.አር 6600 ሰነድ ላይ እየመከረ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
ሰነዱን በተመለከተ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን በዳሰሰው ሳምንታዊ መግለጫቸው ምላሽ የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኤች.አር 6600 በይዘት ደረጃ ሲታይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቀድሞውኑ በኢትዮጵያ የተመለሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ሰነዱ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት እንዲኖርና አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ ሶስቱም እንኳር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ችግር እንደሌለበትና ጥያቄዎቹ እንደተመለሱ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በውስጡ ያሉ ተቃርኖዎች ለመፍታት በሚል ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ማመቻቸቱ ሌለው የውጭ አካላት በበጎ መልኩ ሊመለከቱት የሚገባ እርምጃ ነውም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
አምባሳደር ዲና በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና በምክትላቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመሩ ልዑካን ቡድኖች፤ በቤልጂዬም ብራሰልስ እና በጀርመን ሙኒክ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማራመድ መቻላቸውንም በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስብሰባው በሻገር ከተለያዩ መሪዎች ጋር በነበሯቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያን እውነታ ለማሳወቅ ያቻሉበት፣ ከሀገራቱ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩበት ሁኔታ የመከሩበት እንዲሁም አውሮፓ እና አፍሪካ በጋራ ለመስራት የሚያስችሏቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉ ለማየት የቻሉበት ውጤታማ ቆይታ ነበርም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ከአውሮፓ-አፍሪካ ህብረት ስብሰባ ባሻገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ሙስና፣ በእውቀት ሽግግርና ሰላምና ደህንነት ላይ ያተኮረው 8ኛው የሙኒክ የጸጥታ ኮንፍረንስ መካሄዱን እና ኢትዮጵያ በመድረኩ ጉልህ ተሳትፎ ማድረጓንም አንስተዋል፡፡
በውይይቱ በአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጠና ሽብርተኝነትን መከላከል፣ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገልጿልም ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድና በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደትና ሰላማዊ ሁኔታ በመፍጠር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል አለም አቀፍ ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተመክሮበታልም ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች፣ የተበላሸ ምርጫ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረጋቸውን ኢትዮጵያ አስረድታለችም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ቀንድ በትራንስፖርት በማስተሳሰር የመሪነት ሚና እንዳላት እየታወቀ እንደፈረንጆቹ በ2019 ከተመሰረተው የቀይ ባህር ፎረም ውጭ መሆኗ ተገቢ አለመሆኑን ማስረዳቷንም ጭምር አንስቷል፡፡
“በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በህወሓት ተንኳሽነት መሆኑን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳውቃለች፤ ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ ያስፈልገዋል” መባሉንም ገልጸዋል።