“ድርድር ብዬ የማስበው ብሔራዊ ምክክሩን ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
አማራጭ ሃሳቦች ሊኖራቸው ይችላል ያሏቸው ተቃዋሚ አካላት እድሉን እንዲጠቀሙበትም ጥሪ አቅርበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክክሩ ስምምነት ላይ የማይደረስባቸው ጉዳዮች በሪፈረንደም እልባት እንደሚያገኙ ተናግረዋል
ድርድር ብለው የሚያስቡት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመድረግ የታሰበውን ብሔራዊ ምክክር እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
የሰላም አማራጮችን ለመፈለግ መወያየትና መነጋገሩ እንደማይከፋ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ምንም ዐይነት ድርድር እንደሌለ ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ/ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በምክር ቤቱ አባላት በተነሱ ጥያቄዎችና በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡
እስረኞች መፈታታቸውን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስረኞቹ ዘላቂ ሰላምን፣ የታሳሪዎቹን ሁኔታ እና የተገኘውን ድል ለማጽናትና የጦርነቱን መጥፎ ጎኖች በማሰብ መፈታታቸውን የገለጹ ሲሆን የህግ ክፍተቶች እንደሌሉትና ከእርምጃው ኢትዮጵያ ብዙ ተጨባጭ ጥቅሞችን ማግኘቷን ተናግረዋል፡፡
ድርድርን በመተለከተ ባሰጡት ማብራሪያ ድርድር ማለት እርቅ እንዳይደለ የገለጹ ሲሆን ህወሓት ቀልብ ለመግዛትና ከጦርነት የሚገኝ ምንም ዐይነት ጥቅም እንደሌለ ለመቀበል ከቻለ የሰላም አማራጮችን መፈለጉ እንደማይጎዳ ተናግረዋል፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚደረግ የሚደረግ ምንም ዐይነት ድርድር እንደሌለ በመጠቆም፡፡
ለሰላም ለተስፋ እድል ለመስጠት በሚል እስረኞቹ መለቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ድርድር ብለው የሚያስቡት የታሰበውን ብሔራዊ ምክክር እንደሆነ የተናገሩም ሲሆን የኮሚሽነሮችን የምርጫ ሂደት ያዘጋጀው ምክር ቤቱ ካስፈለገ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነሮቹ ሁሉም ሊወያይና ሊነጋገር የሚችልባቸውን መደላድሎች የመፍጠር ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸውም ውሳኔው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡ ስምምነት ላይ መድረስ የማይቻልባቸው ጉዳዮች በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት እንደሚያገኙም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት፡፡
ጉዳዩ ቅቡልነት እንዲኖረው ሂደቱ ግልጽ፣ አካታች እና አሳታፊ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፤ አጋጣሚውን መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ኮሚሽኑ የጾታ፣ የሃይማኖትና የብሔር ስብጥር ኖሮት በምክር ቤቱ እንዲቋቋም መደረጉንም አወድሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓት የአፋር ክልልን ዳግም መውረሩ ወደ ትግራይ የሚያቀኑ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማስተጓጎል ነው ብለዋል፡፡ በአፋርም ሆነ በአማራ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የኢትየጵያ ጥቃቶች ናቸው ያሉም ሲሆን ከክልል መንግስታቱ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሸኔ ታጣቂዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እና የሚፈጽሙት ጥቃት በወታደራዊ ስራ ብቻ የምላሽ የሚያገኝ እንዳልሆነም ነው ዶ/ር ዐቢይ የተናገሩት፡፡ ይልቁንም ህዝቡ ለምን ሊሸከማቸውና ሊሸሽጋቸው እንደቻለ መጠየቅና ማነጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገር ችግር ላይ በወደቀችበት ጊዜ ባላቸው ዐቅም ተጋድሎ ያደረጉ ልዩ ኃይሎች ጉዳይ በራሱ ችግር አይደለም ብለዋል፡፡ ሆኖም ያለፈ ችግር እንዳይኖረው በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠትና ልክ በፌዴራል ደረጃ እየተሰራ እንዳለ የተሳካ ስራ ሁሉ የጸጥታ ተቋማቱን በአዲስ መልክ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ አስቀምጠዋል፡፡
በሶማሊያ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያጋጠመውና ከፍተኛ ጉዳትን ያደረሰው አስከፊ የድርቅ ሁኔታም አብራርተዋል ዶ/ር ዐቢይ፡፡ በድርቁ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆኑ ዕለታዊ እርዳተዎች፤ ውሃ እና የከብቶች መኖ እየቀረቡ መሆኑን የተናገሩም ሲሆን እስካሁን 750 ሺ ኩንታል ገደማ የዕለት ደራሽ ምግብ መቅረቡንና በተለይ በእንስሳት ሃብት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰውን ይህን ችግር መልክ ለማስያዝና በዘላቂነት ለመቋቋም በውሃ አስተዳደር እና በገበያ ትስስር ረገድ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡