የኢትዮጵያ ደህንነት ይመለከተናል የሚሉ ኃይሎች ህወሓትን ከሽብር ሰርዙ እያሉ ነው- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ከሽብርተኝነት መሰረዝ ላይም ይሁን ድርድር በሚባለው ጉዳይ ላይ እስካሁን የተወሰነ ነገር ብለዋል።
መንግስት ከህወሓት ጋር ይደራደር በማለት የሚያነሱ አካላት መኖራቸውንም አስታውቀዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ካነሱት ጉዳዮች መካከልም፤ “ህወሓትን ከአሸባሪነት የመሰረዝ ጉዳይን የኢትዮጵያ ደህንነት ይመለከተናል የሚሉ ሃይሎች እያነሱት ነው፤ እስካሁን ግን የተወሰነ ነገር የለም” ብለዋል።
“እነዚህ ሀይሎች ከህወሓት ጋር ተደራደሩ እያሉን ነው” ያሉት አምባሳደር ዲና፤ “እኛ ለምን እንደዚህ አላችሁ አንልም፣ የራሳችንን ሃሳብ ነው የምንሰጠው፣ በዚህ ላይ መንግስት የወሰደው አቋም አለ” ሲሉም ተናግረዋል።
መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ አካሂደዋለሁ ያለው ምክክር በህዝብ እና በልሂቃን መካከል መግባባት ለመፍጠር እንጅ በሽብርተኝነት ከተፈረጁት(ህወሓት እና ሸኔ) ቡድን ጋር ለመደራደር አለመሆኑን መግለጹም ይታወሳል።
ህወሓት ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ከመንግስት ጋር በሌላ አካል በኩል እየተነጋገረ መሆኑን ቢገልጽም፣ መንግስት ግን ከህወሓት ጋር ድርድርም ሆነ ንግግር አልጀመርኩም ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አክለውም፤ የተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መምከራቸውንም አስታውቀዋል።
በዉይየቱ ወቅትም የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ስብሰባዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥረው እንደነበር ለምክክል ዋና ጸሃፊዋ ገለጻ ተደርጎ እንደነበረ ገልጸዋል
ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በድርቅ ለተጎዳው ህዝብብ ድጋፍ እንዲሰጥም አቶ ደመቀ ለምክክል ዋና ጸሃፊዋ ጠይቀዋል ብለዋል።
አምባደር ዲና በመግለጫቸው፤ የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፈው ኤች አር 6600 የተሰኘው የውሳኔ ኃሳብን በተመለከተም፤ “የውሳኔ ሀሳቡ ቀረበው በኮንግረስ ነው፣ እኛ ግን ስለመቀራረብ እያወራን ያለነው ከአስተዳደሩ ጋር ነው” ብለዋል።
በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም፤ ሳዑዲ አረቢያ ሄዶ የነበረው ልዑክ የዜጎች ስቃይን በተመለከተ ከተለያ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ መመለሱን አስታውቀዋል።
መንግስት ዜጎችን የመመለስ ግደታ አለበት ያሉት አምባሳደር ዲና፤ መንግስት ለዚህ ልምድ እንዳለው እና በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም እዲመጡ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በሳዑዲ አረቢያ እና በኢትዮጵያ መካካል የሚኖር ግንኙት ዙሪያም “በእሰር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ካስወጣን በኋላ እናወራለን” ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮ ሱዳን ግንኙነትን በተመለከተም የመተማ ጋላባት መንገድ እንዲከፈት፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ውይይት አድርገዋል ብለዋል።
የሱዳን መንግስት ወደዚህ በሚመለሱ ዜጎች ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና እንዲያነሳ እንዲሁም በድንበርና የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ንግግር ውይይት መደረጉንም አስታውቀዋል።