ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩ 11 ግለሰቦች ሹመት ጸደቀ
ከአሁን ቀደም በተለያዩ መንገዶች በተጠቆሙ 42 እጩ ኮሚሽነሮች ላይ የሕዝብ አስተያየት መሰጠቱ ይታወሳል
ሹመቱ ዛሬ ልዩ ስብሰባውን ባደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የጸደቀው
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመውን ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚመሩ 11 ግለሰቦች ሹመት ጸደቀ፡፡
ሹመቱ ዛሬ ልዩ ስብሰባውን ባደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው በ5 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ የጸደቀው፡፡
ፕ/ር መስፍን አርዓያ ዋና ኮሚሽነር ሆነው ሲሾሙ ወ/ሮ ሂሩት ገብረ ሥላሴ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል።
ምክር ቤቱ ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌቱ፣ አምባሳደር አይሮሪት መሃመድ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ብሌን ገብረመድህን፣ ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፣ አቶ ዘገየ አስፋው፣ አቶ መላኩ ወልደ ማርያም፣ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፣ አቶ ሙሉጌታ አጎ እና ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶንም ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል እንደ ኢቲቪ ዘገባ።
ኮሚሽነሮቹ ከአሁን ቀደም በተለያዩ አግባቦች ከተጠቆሙ 42 እጩ ኮሚሽነሮች መካከል ነው የተመረጡት፡፡ በ42ቱ እጩ ኮሚሽነሮች ላይ እስከ የካቲት 1 ቀን 2ዐ14 ዓ/ም የዘለቀ የአምስት ተከታታይ ቀናት አስተያየት ሲሰጥ መቆየቱ እና የሕዝብ አስተያየት (ፐብሊክ ሂሪንግ) መድረክ ምክክር መደረጉ ይታወሳል፡፡
በሕዝብ አስተያየት መድረኩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፋ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ "የኮሚሽነሮቹ ምርጫ ኢትዮጵያዊ ብዝሃነትን ያካተተ እንዲሆን ተሞክሯል" በሚል መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ሃገራዊ ምክክሩን እንደሚመሩ ተስፋ የተጣለባቸው እጩ ኮሚሽነሮች የጥቆማ እና ምርጫ ሂደት ግልጽነት ይጎድለዋል የሚሉ ትችቶችን እያስተናገደ ነው፡፡
ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) እጩ ኮሚሽነሮቹ የተመረጡበት መስፈርት “ራሱ ገዥው ፓርቲ አባል የሆነበት የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ‘ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መሥፈርቶች’ በሚል የቀረበው መስፈርት የጣሰ ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ኮሚሽኑን የማቋቋሙ ሂደት ግልጽነት፣ ገለልተኛ እና አካታች እንደሚጎድለውም ነው የተናገሩት፡፡