የሙሌት አተገባበር የቴክኒክ ሰነዱን ለመመልከት ሁለቱም ፍቃደኛ አይደሉምም ተብሏል
የዋሽንግተኑ መድረክ ለውይይት ክፍት ካልሆነ በስተቀር ወደ መድረኩ እንደማትመለስ ኢትዮጵያ አስታወቀች
የታችኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ያካተተው የዋሽንግተኑ መድረክ ለውይይት ክፍት ካልሆነ በስተቀር ወደ መድረኩ እንደማትመለስ ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡
የመጀመርያውን ሙሌት ማስጀመርን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በግብፅም ሆነ በሱዳን በኩል ስምምነት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የሙሌት አተገባበሩን በተመለከተ የተዘጋጀው የቴክኒክ ሰነድ እንዲላክላቸውና እንዲመለከቱት ቢጠየቁም በሁለቱም በኩል ፍቃደኝነት አለመኖሩ ተጠቁሟል።
ኢቢሲ እንደዘገበው ከሆነ ኢትዮጵያ አሁንም የሶስትዮሽ ድርድሩ ቀድሞ በተቀመጡ መርሆች ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲቀጥል ፍላጎት አላት።
ቀድሞ የምታራምድ የነበረውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደምትቀጥልም አስታውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመሩት ግድቡን የተመለከተ ውይይት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ከሚመለከታቸው አካላት፣ምሁራንና ህዝብ ጋር ልምከር በሚል ባለፉት ወራት ሲካሄድ በነበረው የዋሽንግተን የድርድር መድረክ መገባደጃ ላይ የቀረበውን የስምምነት ሰነድ ሳትፈርም መቅረቷ የሚታወስ ነው፡፡
የውይይት መድረኩ አዘጋጆች አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት እና የስምምነት ሰነድ አዘጋጅነት የተሸጋገሩበት መንገድ በኢትዮጵያ በኩል የገለልተኝነት ጥያቄ እንደተነሳበትም አይዘነጋም፡፡
ግድቡ ሳገኝ የነበረውን ዓመታዊ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል በሙሌቱና በቴክኒካዊ የአተገባበር ሁኔታዎች ላይ ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር ስትደራደር የቆየችው ግብጽ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት ልትጀምር አይገባም በሚል አቤቱታዋን ከሰሞኑ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሰማቷም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ሙሌቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲተገበር ዝግጅቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ያስታወቀችው ኢትዮጵያ በበኩሏ ለአቤቱታው ተገቢውን የምላሽ ሰነድ ማዘጋጀቷን ገልጻለች።