የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል
ብዙዎቹ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የሚያስታውቁ እና የአሜሪካን ገለልተኛነት የሚያጠይቁ ናቸው
የምስራቅ አፍሪካ ህዝብ የሚጠብቀው ሚዛናዊና የማታዳላ አሜሪካን ነው -ዘርሁን አበበ፣የግድቡ ተደራዳሪ
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ዛሬ ያወጣው መግለጫ በርካቶችን እያነጋገረ ነው፡፡
የምክር ቤቱ መግለጫ ልክ ከአሁን ቀደም በዋሽንግተን እንደተስተዋለው ሁሉ የአሜሪካን ወገንተኝነት እና አድሏዊ አካሄድ እንዲሁም የሚዛናዊነት ችግር ያሳየ ነው በሚልም ብዙዎች ተችተውታል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ ሉዓላዊ ግዛት የሚመነጨውን ተፈጥሯዊ ሃብት የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት የጠቀሱ በርካቶችም የሌሎችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ የዜጎቿን ህይወት ለመቀየር እንደምትችል በመጠቆምም ለምክር ቤቱ መግለጫ አጸፋዊ ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨባጭ ያለው ምንድነው?
መግለጫው በምክር ቤቱ ይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጽ በአጭሩ የሰፈረ ነው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ 257 ሚሊዬን ህዝብ ኢትዮጵያ ጠንካራ አመራር እንድታሳይ ይጠብቃል በሚል የሚነበበው የምክር ቤቱ መግለጫ ይህም ከፍትሃዊ ስምምነት ላይ መድረስ ማለት ነው ሲል ይቀጥላል፡፡
መግለጫው የቴክኒክ ጉዳዮች መፈታታቸውን የሚጠቅስም ሲሆን የጉዳዮቹ መፈታት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ጊዜን ለማግኘት እንደሚረዳ ይጠቁማል፡፡
‘የግድቡ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ሶስቱ ሃገራት ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው’ የሚለው ይህ የአሜሪካ ሃሳብ ከአሁን ቀደም በዋሽንግተን በነበረው የድርድር ሂደት ጭምር የተንጸባረቀ ነው፡፡
ሆኖም የዋሽንግተንን ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ከዛም ወደ የስምምት ሃሳብ አርቃቂነት መድረስ ያልተቀበለችው ኢትዮጵያ ከህዝቧ ተወያይታ ወደ ድርድር እንደምትመለስ በመጥቀስ ከድርድሩ መውጣቷ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያውያን ስለ መግለጫው ምን አሉ? ምንስ የአጸፋ ምላሾች ተሰጡ?
ይህ የምክር ቤቱ መግለጫ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል፡፡ በሚያነሱት ሃሳብ እና በሚጠቅሱት እውነታ የተለያዩ ለ3 ሺ የተጠጉ አስተያየቶችንም አስተናግዷል፡፡ 900 ገደማ የሚደርሱ የማህበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎችም መልሰው አጋርተውታል፡፡
ብዙዎቹ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የሚያስታውቁ እና የአሜሪካን ገለልተኛነት የሚያጠይቁ ናቸው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ህዝብ ተብሎ በመግለጫው ከተጠቀሰው ሩብ ቢሊዬን ህዝብ ቁጥር ውስጥ ከ100 ሚሊዬን በላይ የሚሆነው በኢትዮጵያ እንደሚኖርና አብዛኛው መሰረታዊ የሃይል አቅርቦት ሳይኖረው በጨለማ ውስጥ እንደሚገኝ አሜሪካ ለምን ማስታወስ እንዳልፈለገች አበክረው የሚያጠይቁም ጥቂት አይደሉም፡፡
በቅርቡ ለፓርላማ አባላት ማብራሪያን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በርካታ ኢትዮጵያውያን እናቶች በችግር ውስጥ መሆናቸውን በመጠቆም “የእናቶቻችን ወገብ አይጉበጥ ማለት መሰረታዊ መብታችን ነው” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የግድቡ ተደራዳሪ የሆኑት አቶ ዘርሁን አበበ አስተያየታቸውን ካሰፈሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ከግድቡ እና ከድርድሩ ሂደት ጋር በተያያዘ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት አቶ ዘሪሁን 257 ሚሊዬኑ የምስራቅ አፍሪካ ህዝብ የሚያየው ሚዛናዊና የማታዳላ ሶስቱም ሃገራት አሸናፊ ሊሆኑ ከሚችሉበት የስምምነት ደረጃ የሚያደርስ ግብብነት እንዲኖራቸው የምታበረታታ አሜሪካን ነው ሲሉ ምላሻቸውን አስፍረዋል፡፡
ሚሊዬኖችን ከድህነት ለማውጣት በሚያስችል መልኩ የግድቡ ሙሌት በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እንደሚቀጥልም ነው ተደራዳሪው የገለጹት፡፡
በህገመንግስት እና በፌዴራሊዝም ጉዳዮች ላይ ምሁራዊ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እንዲሁም የዩኒቨርስቲው የፌዴራሊዝም ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዘመልዓክ አይተነው (ዶ/ር) በበኩላቸው ‘ትርጉም አልባ’ ሲሉ መግለጫውን አጣጥለውታል፡፡
ግድቡ በስምምነትም ሆነ ከስምምነት ውጪ ሊሞላ እንደሚችል ያስቀመጡም ሲሆን ስምምነት ካስፈለገ የመስማማቱ ጉዳይ የግብጽ እንደሆነና ይህም ተሞክሮ እንዳልተሳካ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤትም መግለጫውን በተመለከተ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አሜሪካ በግልጽ ለግብጽ ማድላቷን እወቁልኝ ሲል በይፋዊ ትዊተር ገጹ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ባያያዘው መልዕክት ያስታወቀው ምክር ቤቱ በግልጽ የአንድን ወገን ፍላጎት ብቻ እያንጸባረቀች እንደ ገለልተኛ ታዛቢ አካል ልትቆጠር እንደማትችልም ገልጿል፡፡
ሚዛናዊም ገለልተኛም አይደለም ያለውን መግለጫ የሚያሳዝን ነው ያለም ሲሆን የአሜሪካ መንግስት ሃገራቱ በፍትሃዊነት መርሆዎች ላይ ተመስርተው ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ለማድረግ የሚያስችል አበረታች አመራር የሚያሳይበት ጊዜ አሁን ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መግለጫውን በተመለከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎቹ ተደራዳሪ ሃገራት የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡