አቶ ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ተወሰነ
በችሎቱ የተገኙት ዳኞች በ2/3ኛ ድምጽ ነው አቶ ልደቱ በዋስ እንዲፈቱ የወሰኑት
አቶ ልደቱን ዛሬ ለማስፈታት የዋስትና ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል
አቶ ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ተወሰነ
አቶ ልደቱ አያሌውን አንድ ህገ ወጥ ሽጉጥ በብርበራ አግኝቼባቸዋለው በሚል አቃቤህግ በከሰሰው አዲስ ክስ አዳማ በሚገኘው ምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ጉዳያቸው ባለፈው ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም መታየቱ ይታወቃል፡፡
ጉዳያቸውን ያየውም ፍርድ ቤት ከአቶ ልደቱ ጠበቆች በኩል ከልብ ህመማቸው ጋር ተያይዞ ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ይደረግ ብለው በጠየቁት ጥያቄ ላይ አከራክሮ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት ዉሳኔ ለመስጠት በያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዉሳኔ አስተላልፏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በዉሳኔው የአቶ ልደቱን የዋስትና ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን 100 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን ዉጭ ሆነው እንዲከታተሉ ማዘዙን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
አቃቤ ህግ አቶ ልደቱ በዋስ ቢወጡ ውጭ የህክምና ቀጠሮ ስላላቸው ሄደው ይቀሩብኛል በሚል ያቀረበው መከራከሪያ የዋስትና ገንዘቡ ከፍ እንዲል ምክንያት እንደሆነ አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡ ዉሳኔውን የዕለቱ ዳኞች 2/3ኛ በሆነ ድምጽ ማጽደቃቸውንም ነው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ለአል ዐይን የገለጹት፡፡
በአሁኑ ወቅት የዋስትና ገንዘቡን በመክፈል አቶ ልደቱን ከእስር ለማስፈታት በሂደት ላይ መሆናቸውንም የገለጹት አቶ አዳነ ፖሊስ ተቃውሞ እንዳላቀረበ እና ዛሬ ከእስር ተለቀው ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ለአል ዐይን በስልክ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ መገደል ተከትሎ በቢሾፍቱ ሁከት በማስነሳት እና በሌሎች ጉዳዮች ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የነበሩት፡፡