አቶ ልደቱ ዛሬ ረፋድ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል
አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው “ቢሾፍቱ ከተማ ላይ የተቀሰቀሰውን ቀውስ አስተባብረሃል ፤ በገንዘብም በመደገፍ ተጠርጥረሃል” የሚል የፍርድ ቤት መጥሪያ በያዙ የፌደራል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲያቸው አስታውቋል፡፡
አቶ ልደቱ ዛሬ ከ 4 ሰዓት በኋላ “የቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ብጥብጥን አስተባብረዋል” በሚል በፌደራል ፖሊስ አዲስ አበባ ላይ ተይዘው ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፈው ሊሰጡ ወደ ቢሾፍቱ እየተወሰዱ እንደሆነ በስልክ ደውለው እንዳሳወቋቸው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ኢዴፓን ጨምሮ ሶስት ፓርቲዎች በጥምረት የመሰረቱት አብሮነት በለውጡ መንግስት ላይ በግልጽ ‘ትችት ሲሰነዝር’ መቆየቱን የተናገሩት አቶ አዳነ “አቶ ልደቱ የታሰሩበት ምክንያትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ” ነው የገለጹት፡፡
“አቶ ልደቱ በእስካሁን የፖለቲካ ትግላቸው አመጽን አነሳስተውም ሆነ በገንዘብ ደግፈው አያውቁም” ያሉት አቶ አዳነ “የተጠረጠሩበት ወንጀል ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፡፡
“ኢዴፓም ይሁን አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ሀገራዊ ለውጡ ተቀልብሷል” የሚል አቋም እንዳለው በመጥቀስ “ይህንን የፓርቲውን እና የጥምረቱን ሀሳብ የሚያስተጋቡ ግለሰቦችን በማሰር መንግስት ፓርቲዉን ለማዳከም እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም ከቀናት በፊት የአብሮነት አባላት ከሆኑ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መታሰራቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ኢንጂነር ይልቃል ከጥቂት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት አዲስ አበባ ዉስጥ በተከሰተው ብጥብጥ ለጠፋው ህይወት እና ንብረት እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው ነው፡፡
“አብሮነትን ለማዳከም በመንግስት ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ” የሚል ግምት እንዳላቸውም የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን በስልክ ገልጸዋል፡፡
“የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማዳከም እርምጃ እየተወሰደ ነው” በሚል የሚቀርቡ ክሶችን የማይቀበለው መንግስት “ግለሰቦቹ ማንም ይሁኑ በወንጀል የሚጠረጠሩ እና በወንጀል ተግባር የተሳተፉ ግለሰቦችን” በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ለፍርድ ማቅረቡን እንደሚቀጥልበት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡
ስለ አቶ ልደቱ መታሰር እና ስለተጠረጠሩበት ወንጀል ነገ አሊያም ከነገ ወዲያ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ዝርዝር መረጃዎች እንደሚታወቁም ነው አቶ አዳነ የተናገሩት፡፡
በርካታ አመታትን በፖለቲካ ዉስጥ ያሳለፉት አቶ ልደቱ አያሌው የኢዴፓ ብሔራዊ ም/ቤት አባል እና የአብሮነት አስተባባሪ ናቸው፡፡
የዝነኛውን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡
ከፖለቲከኞች ባለፈ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትንሹ 239 ለሚሆኑ ሰዎች ሞት እና ለበርካታ የንብረት ዉድመት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዉለው የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው የክስ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ከፍተኛ ዉድመት በደረሰበት በሻሸመኔ ከተማና በምእራብ አርሲ በ10 ወረዳዎች በሁከትና አመጽ ወንጀል የተጠረጠሩ 1 ሺ 523 ግለሰቦች ትናንት ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል፡፡