ፍርድ ቤቱ ለአቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄ ውሳኔ ለመስጠት ለቀጣዩ ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
አቃቤ ህግ አቶ ልደቱ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው ያቀረበው መከራከሪያ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል
አቶ ልደቱ ዛሬ አዳማ በሚገኘው ምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ጉዳያቸው ታይቷል
ፍርድ ቤቱ ለአቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄ ውሳኔ ለመስጠት ለቀጣዩ ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
አቶ ልደቱ አንድ ህገ ወጥ ሽጉጥ በብርበራ አግኝቼባቸዋለው በሚል በከሰሰው አዲስ ክስ ችሎት ስለመቅረባቸው ነው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ችሎት የገለጹት። ጉዳያቸውን ያየውም ፍርድ ቤት ከአቶ ልደቱ ጠበቆች በኩል ከልብ ህመማቸው ጋር ተያይዞ ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ይደረግ ብለው በጠየቁት ጥያቄ ላይ አከራክሯል።
አቃቤ ህግ በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን ያስፈራራብኛል፣ ውጭ የህክምና ቀጠሮ ስላላቸው ሄደው ይቀሩብኛል በሚል ዋስትናውን ተቃውሟል። ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ጉዳይ ተከሳሽ ጉዳዪን ባልካዱበት ሁኔታ ምስክሮችን ሊያስፈራራ የሚችልበት ሁኔታ የለም በሚል ውድቅ እንዳደረገባቸው ከኢዴፓ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውጭ የህክምና ቀጠሮአቸውን በተመለከተ አቶ ልደቱ ሃሳብ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸው አስተያየት ስለመስጠታቸውም ተገልጿል።
አቶ ልደቱ በሰጡት አስተያየት “ፌደራል ትፈለጋለህ ባለኝ ግዜ ሄጄ እጄን የሰጠው ሰው እንዴት ከህግ ልሸሽ እችላለሁ፣ እኔ ከልብ ህመሜ ጋር ተያይዞ የማቀርበው የዋስትና ጥያቄ በህይወት የመኖር እና ያለመኖር ነው። …ስለዚህ ውጭ ሄጄ መታከም ህጉ ስለማይከለክል በህይወት ለመቆየት ዋስትና ተፈቅዶልኝ እንድታከም ቢደረግ፣ ይህ እንኳን ቢቀር በህይወት ለመቆየት የሀገር ውስጥ ህክምና እንድከታተል እና ለኮሮና ተጋላጭ ከሆንኩበት ሁኔታ ልወጣ ይገባል” ብለዋል።“በተጨማሪም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጬ ጠበቆቼን አሰናብቼ ነበር። ነገር ግን በጠበቆቼ ግፊት፣ አዲስ ችሎት እና አዲስ ዳኞች በመሆናችሁ ፍትህን ከናንተ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ” በሚል ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም ሰኞ በጉዳዩ ላይ መክሮ ውሳኔ ለመስጠት ለማክሰኞ ከሰዓት 8 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
ዛሬ ለአቶ ልደቱ ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን፣ መሀመድ ጅማ እና ገመቹ ጉተማ ከጎናቸው ሆነው በነፃ እንደተከራከሩላቸውም አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡