15 የመከላከያ አባላት ከደ/ሱዳን “ወደ ኢትዮጵያ አንሄድም“ ማለታቸው የሰራዊቱን እና የሀገርን ስምና ዝና ለማጠልሸት ታልሞ የተደረገ ነው ተባለ
በደ/ሱዳን ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች 15ቱ “ለህይወታችን ያሰጋናል“ በሚል ጁባ መቅረታቸውን ተመድ አስታውቋል
መከላከያ እንዳለው ወታደሮቹ ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በመንከባለልና በመጮህ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ፣ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሆነው ሲያገለግሉ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 15 የትግራይ ተወላጆች “ለህይወታችን ያሰጋናል“ በሚል ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዳልፈለጉ ትናንት አስታውቋል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ 169 ከኢትዮጵያ የተመደቡ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በተለመደው አሰራር መሠረት ከጁባ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በአዲስ ሰራዊት ይተኩ እንደነበር አንስተዋል። ከነዚህም 15 ወታደሮች ከጁባ ኤርፖርት ለመሳፈር ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጸው ዓለም አቀፍ ጥበቃ የሚያስፈልገው ማንኛውም ሰው ጥገኝነት የመጠየቅ መብት አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
15 የሠራዊት አባላት “ወደ ሀገራችን አንሄድም“ ማለታቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም አንመለስም ያሉት ወታደሮች በደቡብ ሱዳን ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ “በመንከባለልና በመጮህ ሁከት ለመፍጠር መሞከራቸውን” አስታውቋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት እና የሀገርን መልካም ስምና ዝና ለማጠልሸት ታልሞ የተደረገ እንደሆነ የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜ/ጄ መሐመድ ተሰማ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ አኩሪ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ቦታዎች ተቀጥረው የሚሰሩ “ትግሪኛ ተናጋሪዎች” የሰራዊት አባላት UNHCR የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ በማመቻቸት ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲሰማው ለማደረግ የተሞከረ እንደነበር ሜ/ጄ መሐመድ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ያስተጋባው ዘገባ ያልተገባ በመሆኑ ይቅርታ ሊጠይቅ” እንደሚገባ ሜ/ጄ መሀመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡
በግለሰቦች እንዲህ አይነት ድርጊት መፈፀሙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የማይወክልና የግለሰቦች ብቻ እንደሆነ ነው ሜ/ጄ መሀመድ የገለጹት፡፡