አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በጌዴኦ ‘ደራሮ’ በዓል ላይ ተገኝቶ መልዕክት አስተላለፈ
ከዚህ ቀደም ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ የጌዴኦ ተወላጆች ገቢ ያሰባሰበው ታማኝ “ከተባበርን ማንኛውንም ችግር መሻገር እንችላለን” ብሏል
የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ደራሮ’ በዲላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል
የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ደራሮ’ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በዲላ ከተማ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል፡፡ በዓሉ የመኸር ምርት ከተሰበሰበ በኋላ የሚከበር የምስጋና በዓል ነው፡፡
ህብረተሰቡ የዘራውን ላሳጨደው ፣ ዓመቱንም ከክፉ ለጠበቀው ፈጣሪው ከሚያቀርበው ምስጋና በተጨማሪ ቀጣዩን ዓመት ካለፈው የተሸለ እንዲያደርግለትም ይማጸናል፡፡
በዚህ በዓል ላይ የጌዴኦ ህብረተሰብ ለአባገዳዎች እና ለታላላቅ ሰዎች በመኸር ከሰበሰበው ምርቱ ያሻውን ያህል እንደመሻቱ ቆርሶ ስጦታም ያቀርባል፡፡
በጌዴኦ የተለያዩ አካባቢዎች የበዓሉ ሥነ ስርዓት ለአንድ ወር ያህል ሲከናወን ቆይቶ ዛሬ በዲላ ማጠቃለያው እና ዋናው የበዓል ሥነ ስርዓት ተካሒዷል፡፡
በዲላ ከተማ በመገኘት ከህብረተሰቡ ጋር የደራሮ በዓልን ያከበረው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ኢትዮጵያውያን “ከተባበርን ማንኛውንም አይነት ችግር መሻገር እንችላለን” ሲል ተናግሯል፡፡
አርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው “ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ” ከሁለት ዓመታት በፊት ከኦሮሚያ ክልል በተለይ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ የጌዴኦ ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ጥረት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ተቋሙ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከህብረተሰቡና ከመንግስት ምስጋና ተችሮታል፡፡
አርቲስት ታማኝ ዛሬ ዲላ ላይ ባደረገው ንግግር የጌዴኦ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ለቀረበው ጥሪ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን አስደናቂ ምላሽ መስጠታቸውን በማስታወስ በዜጎች ትብብር የበርካቶችን ህይወት ወደ ቀድሞው ለመመለስ መቻሉን ተናግሯል።
አስከፊው ጊዜ አልፎ የጌዴኦ ህዝብ የደራሮን በዓል እንዲህ በድምቀትና በፈንጠዝያ ሲያከብር በመመልከቱ እጅግ መደሰቱንም አርቲስቱ ገልጿል።
በዲላ ስታዲየም የተገኙ በርካታ የበዓሉ ታዳሚያንም ለአርቲስት ታማኝ በየነ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ፣ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እና የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሺፈራው ቦጋለም የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡