በሰዎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ እስርና ጥቃት እንዲቆም ኢሰመኮ ጠየቀ
ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀም የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል
በትግራይ ክልል በኤርትራ ስደተኞች ላይ በህወሓት ኃይሎች እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች አሳሳቢ ናቸው
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ ብሎም በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ፤ በታሳሪዎችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢሰብአዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀም የሚያመላክቱ መረጃዎች “እጅግ” እንደሚያሳስበው ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ “የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተቃዋሚ ናቸው“ በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች የሚያሳስቡ መሆናቸውንም መግለጫው ያብራራው።
ከአላማጣና አካባቢው በድጋሚ ያገረሸውን ግጭትና በመኾኒ እየተወሰዱ ስለመሆናቸውን የሚነገሩ የበቀል ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎች መፈናቀል እያደረሰ ስለመሆኑም ኢሰመኮ ገልጿል።
ቴሌኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራውን አዳጋች እንዳደረገው የተገለጸ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የተደራሽነት ሁኔታ በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል እንደሚቀጥል ጠቅሷል።
በመሆኑም በቆቦ፣ ወልዲያ እና በመርሳ ተጠልለው የሚገኙ ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን ኮሚሽኑ እንደሚጎበኝ ለአል ዐይን በላከው መግለጫ ገልጿል።
ኢሰመኮ፤ የግጭቱ መባባስና የግጭቱ ተጽዕኖ በአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጭምር መስፋፋቱ “እጅግ ያሳስበኛል” ብሏል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚደርሱትንና በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሱ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት እና የእንግልት መረጃዎችንም እየተከታተለ ይገኛል።
የሚድያ ሰራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ለኮሚሽኑ ጥቆማዎች ደርሰውታል።
ከሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተባብሶ የታየው ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ክስተትና እስር ሁኔታ ተገቢውን ትኩረትና መፍትሔ ከአለማግኘቱ በተጨማሪ፤ በስፋት የሚደመጡ የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታውን ሊያባብሱና ብሎም በማሕበረሰብ መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ እንደሚችሉም ኢሰመኮ ጠቅሷል።
በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል መስተዳድሮች በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን በሕግ ፊት እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በዚህ ፈታኝና የውጥረት ወቅት መንግስት ለሲቪል ሰዎችና ተጋላጭ ለሆነው ማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚጣልበት መሆኑን ገልጸዋል።
መሰረታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆች በግጭት ወቅት ጭምር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያዙና ሲቪል ሰዎችና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ላይ ከፍ ያለ ግዴታ የሚጥሉ መሆናቸውም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
ኢሰመኮ፤ ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸውንም መረጃዎች እንደደረሱት ጠቅሷል።
ይህ ጥቃት የደረሰው ከዕለቱ አንድ ቀን አስቀድሞ “ፍየል ውሃ” በሚባል ቦታ “ሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች” በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የሚሊሽያ ቡድን አባላትና የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው ከተነገረ በኋላ መሆኑንም ኮሚሽኑ አንስቷል።
ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋዱን ጉመራ ወንዝ ተብሎ ከሚጠራና ከተገደሉት የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ትውልድ ቦታ የኃላፊውን እሬሳ ለመቀበል የመጡ ነዋሪዎች ጥቃቱን እንዳደረሱም ኢሰመኮ ከደረሰው መረጃ መረዳቱን አካቷል።
የፎገራ ወረዳና የአካባቢው የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎች በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ሁኔታው መረጋጋቱንና ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን የተከሰተው ሁኔታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት እንደሚያሰጋም ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ አካቷል።
ኮሚሽኑ፤ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ስራ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡ በግጭቱ ለሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ እንዲሁም የሚድያ ተቋማትን ጨምሮ ለሀገራዊና ለዓለም አቀፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ ማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግሮች፣ መግለጫዎችና ተግባራት እንዲቆጠቡም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።