ተመድ የህወሓት ኃይሎች የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ “በአስቸኳይና ሙሉ በሙሉ” እንዲደግፉት አሳስበ
የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የህወሓት ኃይሎች የኢትዮጵያ መንግስት ለጣለው ተኩስ አቁም እንዲገዙና “በአስቸኳይና ሙሉ በሙሉ” እንዲደግፉት አሳስቧል፡፡
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ እና ተለዋጭ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ባደረገው ስብሰባ ነው የትግራይ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ የተጠየቀው፡፡የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ የሕወሓት ሃይሎች እስካሁን ተኩስ ለማቆም አለመስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኗን የገለጹት ሮዝመሪ ዲካርሎ በሀገሪቱ “እየሆኑ ያሉት ነገሮች የሚያሳዩት ችግሮች አስተማማኝና በተሟላ መልኩ” መመለስ እንዳለባቸው ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊዋ ከ8 ወራት በኃላ መንግስት በትግራይ የተኩስ አቁም ማወጁንና የትግራይ ኃይሎችም የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ መንግስት ያስተላላፈው የተከስ አቁም ውሳኔ ህወሓትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊጠቀሙበት የሚገባ እድል ነው፤ የህወሓት ኃይሎችም ተኩስ አቁሙን “በአስቸኳይና ሙሉ በሙሉ” ሊደግፉት ይገባል ብለዋል፡፡
በትግራይ አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልጉት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ የገለጹት ኃለፊዋ ሁሉም ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰራተኞች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተናፍረዋል፡፡
በትግራይ የተኩስ አቁሙ መከበር የሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ ብቻ ሳይሆን ከቀወሱ ለመዉጣት ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመፈለግ ያስችላል ብለዋል ኃላፊዋ ሮዝመሪ ዲካርሎ፡፡
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሰኞ የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅና የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ መቀሌና ሌሎች የትግራይ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ወድቀዋል ተብሏል፡፡
በመቀሌ ከተማ የመብራትና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሌለ ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ ዋና ዋና የሚባሉ መሰረተ ልማቶች ከመውደማቸው ውጭ ሁኔታው በአብዛኛው የተረጋጋ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የተናጠል ተከሱ አቁም ያወጃው ለትግራይ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት መሆኑንና ውሳኔው ወታደራዊ አለመሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስትያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በትናንትናው እለት ለዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታትና አዲስ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የህወሃት ኃይሎች ተኩስ ከፍተዋል ሲል ከሷል፡፡