በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ግጭቶች በዋናነት ከሕዳሴ ግድብ ጋር እንደሚያያዙ ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል
“ብልጽግና እንደ ኢህአዴግ በመንግሥት ሥራ እጁን አያስገባም” ጠ/ሚ ዐቢይ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ቀደም ሲል ገዥ ከነበረው ኢህአዴግ አኳያ ሲታይ በመንግስት ሥራዎች ላይ እጁን እንደማያስገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡
አንዲት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መንግስታቸው አሀዳዊ ነው በሚል ትችት የሚያቀርቡ መኖራቸውን አስመልክቶ ላቀረበችላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ብልጽግና እንደ ኢህአዴግ በመንግሥት ሥራ እጁን አስገብቶ አያንቦጫርቅም” ብለዋል፡፡ ይልቁንም እንደ ፓርቲ የፖለቲካ ሥራ ብቻ እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡
ብልጽግና ሕብረ ብሔራዊ መሆኑ የፌዴራል ሥርዓትን የሚያዳክም እንዳልሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የፌዴራል ስርዓቱ በሕግና በሕገ መንግስት እናንተ በምታወጧቸው አዋጆች ነው የሚመራው ብለዋል፡፡
ፓርቲው ሕብረ ብሔራዊ መሆኑ በሕገ ደንብ እንደሚመራ በማንሳት “ሕገ ደንብ ደግሞ ከሕገ መንግስት ብቻ ሳይሆን ከካቢኔ አባላት ከሚወጡ ደንቦችም ያነሰ ነው” ብለዋል፡፡
“ፌዴራላዊ ማለት ዴሞክራሲያዊ ነው፤ አሀዳዊ ማለት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው በሚል ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች ፖለቲካን ለማያውቁ ሰዎች እያታለልን እንኖራለን የሚሉ የዕለት ጉርሻ ብቻ የሚጎርሱ ሰዎች ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም አሁን ለሚነሳው ሃሳብ አንዱ መሰረታዊ ችግር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ብልጽግና ሕብረ ብሔራዊ መሆኑ ፌዴራላዊ ስርዓትን ያዳክማል ብለው የሚያነሱ ሰዎች እንዳሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፌዴራል ሥርዓት ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅም እና ይህን ስርዓት የማዳከም ፍላጎት እንደሌላቸው ነው ያብራሩት፡፡
ኢህአዴግ ሲመራው የነበረው መንግሰት ፌዴራላዊ ቢሆንም ኢህአዴግ ግን “የዴሞክራሲን ሽታ እንደማያውቀው” በማብራሪያቸው ወቅት አንስተዋል፡፡ በዓለም ላይ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ ሀገራት 28 ብቻ መሆናቸውን በአብነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዚህ ሀገራት ውጭ ያሉት ዴሞክራሲያዊ አይደሉም ማለት ነው ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
እርሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የፌዴራል መንግስት በአንድም ክልል የሥልጣን ድንበር ውስጥ ለአንድ ቀን እንኳን ተሳትፎ እንደማያውቅ አንስተዋል፡፡ ለዚህም ነው “ክልልና ፌዴራል ተብሎ ብዙ የሚነሳው” ብለዋል፡፡
የህግ የበላይነትን እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ከማክበር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ያልሸሸጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ምነም ይሁን ምን የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ማክበር እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መንግሥትን የሚተቹ ግለሰቦችም በነጻነት መተቸት እንዳለባቸው ነገር ግን ክፍተት ካለባቸው ማጣራት እንደሚጠይቅ እንጂ ስለተቹ ማሰር አግባብ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ በመተከል እና ካማሺ አከባቢ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ግጭት በተመለከተ በድርጊቱ በርካታ ተዋንያን ያሉ ቢሆንም ዋናው ጉዳይ ከህዳሴ ግድብ ጋር ይያያዛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡ ድርጊቱ የግድቡን ስራ ለማስተጓጎል ታቅዶ የሚፈጸም እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
በአካባቢው አብዛኛው ጥቃት በቀስት የሚፈጸም መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክአምድሩም አስቸጋሪ እንደመሆኑ ዜጎችን ለመታደግ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መስዋዕትነት ስለመክፈሉ ተናግረዋል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎች እርምጃ ሲወሰድ እየሸሹ ባልተረጋጉ የደቡብ ሱዳን አጎራባች አካባቢዎች ጭምር ሸሽተው ነገሮች ሲሰክኑ ተመልሰው የመምጣታቸው ጉዳይም ሌላው ፈተና እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባለፉት ሳምንታት በተደረገው ኦፕሬሽን ሰፋፊ ድሎች ተመዝግበዋል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተማርከዋል፤ ብዙዎቹ ሸሽተዋል፣ ከሞላ ጎደል አከባቢውን ለማጽዳት ሰፊ ስራ ተሰርቷል” ብለዋል፡፡
“ሰዎች ተደራጅተው፣ ብድርም አግኝተው ሞፈርና መዶሻ እንዲይዙ እንጂ ጦር እና ቀስት እየያዙ፣ ክላሽ እየያዙ እንዲጋደሉ አይደለም ምንፈልገው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
በመጨረሻም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር የድጋፍ ሞሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።