የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረሥላሴ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈጸመ
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አደራጅ ኮሚቴ እና የደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ
ሻምበል ፍቅረሥላሴ ከጳጉሜ 5/1979 እስከ ጥቅምት 29/1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የአየር ኃይልን በመወከል ደርግን ከመሰረቱ ቀዳሚ አባላት መካከል አንዱ የነበሩት ሻምበል ፍቅረሥላሴ በ 75 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ቅዳሜ ዕለት ታህሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ተወካይ ስለሺ መንገሻ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡
ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ከጳጉሜ 5 ቀን 1979 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 29 ቀን 1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ሻምበል ፍቅረሥላሴ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው። በኢትዮጵያ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ወጣት ካዴት ሆነው በመግባት በ1955 ዓ.ም የተመረቁ ሲሆን በአሜሪካም ስልጠና ወስደዋል።
የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ አየር ኃይልን ወክለው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባል እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ሀገራቸውን ያገለገሉት ፍቅረሥላሴ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አደራጅ ኮሚቴ እና የደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ።
"እኛና አብዮቱ” እና "እኔና አብዮቱ” በሚል ርዕስ ሁለት መጽሐፍትን ጽፈው ለአንባቢያን አድርሰዋል።
ፍቅረሥላሴ ወግደረስን ጨምሮ 42 የደርግ አመራሮች በ1989 ዓ.ም በግድያ፣ በዘር ማጥፋት እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን በ2000 ዓ.ም የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በተከሰሱበት ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር።
በ2003 ዓ.ም የፍቅረሥላሴ እና ሌሎች 23 የደርግ አመራሮች የሞት ቅጣት ተነስቶ በ2004 ዓ.ም ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ አይዘነጋም። ሻምበል ፍቅረሥላሴ 20 ዓመታትን በእስር ቆይተዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ ለትውልድ ተሰንዶ እንዲቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንደ ነበሩ በሕይወት ታሪካቸው ተጠቅሷል፡፡