የትራምፕ አስተዳደር ከጉዳዩ ጋር በተያዘዘ ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ድጋፎችን ያዝ የማድረግ ጫን ያለ ፍላጎት አለውም ተብሏል
የግድቡ ጉዳይ በአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል መከፋፈልን ፈጥሯል
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል መከፋፈል መፈጠሩን ፎሬይን ፖሊሲ የተባለው ዓለም አቀፍ መጽሄት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ዋሽንግተን ለግብጽ ያደላ አቋምን ማንጸባረቋ ብዙዎቹን ባለስልጣናት አስግቷል፡፡
ይህም ነው በባለስልጣናነቱ መካከል መከፋፈሉን የፈጠረው፡፡
መከፋፈሉና የባለስልጣናቱ ውዝግብ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጉዳዩን በተመለከተ እንዲያሸማግሏቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕን ከተማጸኑበት ከባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ወዲህ የመጣ ነው፡፡
“አስተዳደሩ ከግብጽ ጎን ለመቆም በሚል እስከጭንቅላቱ ነው ወደ ጉዳዩ የገባበት፤ በ‘ኋይት ሃውስ’ ማንም ጉዳዩን በአፍሪካዊ መነጽር ለማየትና እኩል የሚጠቅመውን የኢትዮጵያን ጉዳይ ለመመልከት አይፈልግም፤ ይህ ደግሞ ራስን በራስ እንደመምታት ነው” ሲሉም ነው የአስተዳደሩን አካሄድ የሚተቹ አንድ ባለስልጣን የሚናገሩት፡፡
ሆኖም የሃገሪቱ ግምጃ ቤት (ትሬዠሪ ዲፓርትመንት) ቃል አቀባይ አድሏዊ የተባለውን የአስተዳደሩን አካሄድ አስተባብለዋል፡፡
በያዘው አቋም በብዙዎች በመተቸት ላይ የሚገኘው የትራምፕ አስተዳደር ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያዘዘ ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ድጋፎችን ያዝ የማድረግ ጫን ያለ ፍላጎት እንዳለውም ነው መጽሄቱ የዘገበው፡፡
በአፍሪካ ህብረት ቢሮ አባላት የተጀመረው የድርድር ሂደት ፍሬያማ እንደነበር ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀሪዎቹ ተደራዳሪ ሃገራት አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከድርድሩ ማግስት (ትናንት ረቡዕ) የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ አብስራለች፡፡
ከአሁን ቀደም የታዛቢነትን ሚና ይዞ ሃገራቱን ለማደራደር ሲሞክር የነበረው አስተዳደሩ ሃገራቱ እንዲፈርሙ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ አቅርቦ ነበር፡፡
ግብጽም ሰነዱን ፈርማ ነበረ፡፡
ሆኖም የአስተዳደሩ ሚና ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪ እንዲሁም የስምምነት ሃሳብ አቅራቢነት መቀየሩን የተቸችው ኢትዮጵያ ከህዝብ ጋር ልምከር በሚል የስምምነቱን ሰነድ ሳትፈርም መቅረቷ ራሷን ከውይይቱ ማግለሏም የሚታወስ ነው፡፡