የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ምእመኖቼ ተገድለውብኛል አለች
ቤተ ክስርቲያኗ በተፈጸመ ጥቃት 8 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መገደላቸውን አሰታውቃለች
5 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ቆስለው ሆስፒታል እንደሚገኙም ገልጻች
የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን “ምእመኖቼ ተገድለውብኛል” አለች።
ቤተ ክስርቲያኗ ባወጣችው መግለጫ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በምትገኝ የሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ስምንት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መገደላቸውን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ሙሉወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት መጋቢ ላኮ በሰጡት መግለጫ፥ ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በቤሮ አጥቢያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት ምእመኖች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱን አስታውቀዋል።
በደረሰው ጥቃት 8 ቤተ ክስርቲያኗ አባላት ሲገደሉ፤ አምስቱ 5 ሰዎች ደግሞ ቆሰለው በሆስፒታል እንደሚገኙ ገልጸዋል።
- መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በቄለም ወለጋ ምእመኖቼ በታጣቂዎች ተገድለውብኛል አለች
- ጨቅላ ህጻንን ጨምሮ 36 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በኦሮሚያ ክልል መገደላቸው ተገለጸ
መጋቢ ላኮ በመግለጫቸው በሌሎች የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ሲጠቀስ የድሮን ጥቃት እንደደረሰ የተዘገበ ቢሆንም መንግስት ድርጊቱ በድሮን የተፈጸመ እንዳልሆነ ነገር ግን በአካባቢው በሚገኙ ታጣቂዎች እንደደረሰ መገለጹ አስታውቀዋል።
“ድርጊቱ በየትኛውም አካል በምንም መልኩ ይፈጸም፥ በንጹሃን ወገኖች ላይ የደረሰውን ጉዳት አጥብቃ እንደምታወግዝና ቤተ ክርስቲያን በጉዳቱ እጅግ ማዘኗንና ጉዳዩ በማን እንደተፈጸመ ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰፍን እንደምትፈልግ” አስረድቷል።
“ገለልተኛ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጉዳዩን በአንክሮ በማየት እንዲያጣሩ፥ እውነቱንም ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ትጠይቃለች” ብሏል መግለጫው።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል መንግስት በዱር ቤቴ እንዲሁም በቡሬ ከተማ በአባሎቿ ላይ የሞት፥ የስደትና የንብረት ጉዳት እየደረሰ እንዳለ በመግለጫው ተጠቅሷል።
በምዕራብ ኢትዮጵያም የአማኞችን ንብረት መውረስና መፈናቀል እየደረስ እንዳለ ይህን የሰብዓዊ መብት መጣስና የዜጎችን ጉዳት የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲያጣራ ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ከዚህ ቀደም በቄለም ወለጋ ዞን 9 ምእመኖቿ በታጣቂዎች በጅምላ እንደተገደሉባት ማስታወቋ ይታወሳል።