መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በቄለም ወለጋ ምእመኖቼ በታጣቂዎች ተገድለውብኛል አለች
ቤተክስርቲያኗ 9 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትላይ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን አሰታውቃለች
ግደያው ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ በቤተ ክርስቲያን በጸሎት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በፈጸሙንም ገልጻች
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በቄለም ወለጋ ዞን ምእመኖቼ በታጣቂዎች ተገድለውብኛል አለች።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በዛሬው እለት ባወጣችው መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፤ መነ ሃሞ በመባል በሚታወቀው ቀበሌ “ቶኩማ መነ ሃሞ” በተሰኘ የመካነ ኢየሱስ ማህበረ ምዕመናን ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል ብላለች።
ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ በቤተ ክርስቲያን በጸሎት ላይ ከነበሩት 17 ሰዎች መካከል 9 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ላይ የጅምላ ግድያ መፈጸሙንም አስታውቃለች።
የጅምላ ድግያ የተፈጸመባቸው ምእመናን ሁሉም በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩና አምስቱ ከሁለት ቤተሰቦች የሆኑ ወንድማማች ሲሆኑ ከዘጠኙ አራቱ የቤተሰብ ኃላፊዎች እንደበሩም አብራረርታለች።
ቤተክርስቲያኗ በመግለጫው ግድያው የተፈጸመው “ማንነታቸው ተጣርቶ ባልታወቀ ታጣቂዎች” ነው ያለች ሲሆን፤ መንግስት ባለው ሃላፊነት መሠረት ሁኔታውን አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል በሚል ተስፋ እስካሁን ዝምታን መርጣ መቆየቷንም ገልጻች።
በነዚህ ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት በሌላቸው ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመ፤ ጭካኔን የተሞላ ዘግናኝ ድርጊትን ቤተ ክርስቲያኒቱ በጽኑ እንደምታወግዝና ኃዘንዋንም ገልጻች።
በጊዳሚ የተከሰተው ይህ የአባላቶቿ በግፍ መገደል በዓይነቱ የመጀመሪያ አይደለም ያለችው ቤተክርስቲያኗ፤ ከዚህም በፊት በተለያዩ ቦታዎች፤ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በምስራቅ ወለጋ በሳሲጋ ወረዳ 15 የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን በዕሁድ የአምልኮ አገልግሎት ላይ እያሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በጅምላ መገደላቸው፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ወረዳ በዕሁድ አምልኮ ላይ የነበሩ ሶስት ወጣቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውሳለች።
እዲሁም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በምእመናን ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተከሰቱ መሆኑን የጠቀሰች ሲሆን፤ ለነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለፍትህ ድምጽዋን ስታሰማ ብትቆይም ምላሽ የተሰጠበት አንድም ጊዜ አልነበረም ብላለች።
የምዕመናኖቻችንን በሕይወት የመኖር ህገ መንግስታዊ መብት ያሳጡትን፤ ማንነታቸው በግልጽ ያልተጣራ የታጠቁ ቡድኖችን ለይቶ ወደ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ያደርግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን መንግስትን ጠይቃለች።