ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲ ጥብቅ አፍሪካዊ መሠረት የያዘ ነው
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲ ጥብቅ አፍሪካዊ መሠረት የያዘ ነው
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ ጥር 8 ቀን 2012 ዓም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሃገር ውስጥ እና ለውጭ ሚዲያዎች ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በጊኒ ሪፐብሊክ፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ እና በደቡብ አፍሪካ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች፣ በቀጣይ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ 26ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጠረፍ አስተዳደሮች ኮሚቴ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ እና ቻይና 50ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል አከባበር ዝግጅትን እና የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቸ የዋሽንግተን ዲሲ ውይይት እና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር የምታራምደው ዲፕሎማሲ ጥብቅ አፍሪካዊ መሠረት የያዘ መሆኑን የገለጹትአቶ ነብያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ3ቱ የአፍሪካ ሃገራት መንግስታት ግብዣ እ.ኤ.አ ከጥር 8 – 12/2020 ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የተሳካ ነበር ያሉት አቶ ነብያት የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር የተቻለበት፣ ከዚህ በፊት የተፈረሙ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ አዳዲስ ስምምነቶች የተፈረሙበት እንዲሁም በየአገራቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚኖሩበት ሁኔታ የተመቻቸበት ነበር ብለዋል፡፡
በተለይም የደቡብ አፍሪካው ጉብኝት የሃገራቱ ግንኙነት ወደ ስልታዊ አጋርነት ያደገበት እና በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ችግር መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት የተደረገበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያውን መብቶች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪይል ራማፎዛ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የሚመራ ኮሚቴ አዋቅረው እርምጃ እንደሚወስዱም ቃል ገብተዋል፡፡
ጤናን፣ ቱሪዝምን እና የዲፕሎማቲክ እንዲሁም የሰርቪስ ፓስፖርት ባለቤቶች የያዙ የሃራቱን ዜጎች ያለ ቪዛ እንቅስቃሴን አስመልክቶም ሶስት የመግባቢያ ሰነዶች ተፈራርመዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከየካቲት 6-10/2020 በአዲስ አበባ የሚካሄደውን 33ኛው መደበኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 36ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አስመልክቶም ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡አጠቃላይ ስብሰባውን የሚመራ ብሄራዊ እና ሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎች በየደረጃው ተቋቁመው ወደ ስራ መገባቱንም አቶ ነብያት ተናግረዋል፡፡
በየ6 ወሩ የሚካሄደው 26ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጠረፍ አስተዳደሮች ኮሚቴ ስብሰባም በጅግጅጋ ከጥር 14-16/2020 ተካዷል፡፡ በስብሰባውም የድንበር ደህንነትን፣ የፀጥታ አስከባሪ አካላት ትብብርን እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታትን እንዲሁም በሁለቱ ሃገራት የሚካሄድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማሳለጥና በመሰል ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ከ1970 ጀምሮ የተመሰረተው የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፈርጀ ብዙ ዘርፎች እያደገና እየተጠናከረ መጥቶ እ.ኤ.አ በ2017 ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እ.ኤ.አ ከጥር 13-15/2020 ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሚኒስትር ቢሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ላይ ያካሄዷቸውን የቴክኒክ ምክክሮች በተመለከተ የአሜሪካና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበት ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ አስቀድመው ባካሄዷቸው የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይ በተነሱ ነጥቦች ውይይት ካካሄዱ በኋላ እስከ ጥር 28 ቀን 2020 ድረስ የቴክኒክ ውይይቶች እንዲቀጥሉ እና ውጤቱ እንዲቀርብ መስማማታቸን፤ በቀጣይ የቴክኒክ ውይይት እልባት ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የውሃ ሙሊት እና አለቃቀቅ ስርዓት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መግባባት እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ከዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲ አንጻር ከጥር 6 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት ውስጥ 238 ኢትዮጵያዊያን ከሌባኖስ ወደ ሀገራቸው እንደሚገቡ አቶ ነብያት ገልጸዋል።