በኢትዮጵያ ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል የሚመደቡት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ ማን ነበሩ?
ከአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነት እስከ ጠቅላይ ሚንስትር አማካሪነት የዘለቀው ህይወታቸው ምን ይመስላል?
የፕሮፌሰሩ ስርአተ ቀብር ነገ እሁድ፣ ጷጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ይፈፀማል
በ1937 ከእናታቸው መንበረ ገብረማርያም እና አባታቸው እሸቴ ተሰማ በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የአራት ኪሎ ልጅ ናቸው፡፡
በሶስት ቤተሰብ ውስጥ እንዳደጉ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ በእነኚህ ቤተሰቦች ውስጥ ማለፋቸው ለነበራቸው ስብእና ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡
ከወላጆቻቸው በተጨማሪ አጎታቸው አቶ ጀማነህ አላብሶ እና በሪቻርድ ፓንክረስት ቤተሰብ ውስጥ ያሳለፉት የልጅነት እና የወጣትነት እድሜ በእውቀት ፣ ንባብ እና ልምድ የጎለመሱበት ነው፡፡
በዳግማዊ ምንሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ህይወታቸውን አንድ ብለው የጀመሩት አንድሪያስ እሸቴ በዊልያምስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ሰፊ የንባብ ልምድና የፍልስፍና ሕይወት ውስጥ አልፈዋል፡፡
ከሀገር ውጪ በተለያዩ ድርጅቶች ከሰሩና በበርካታ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካስተማሩ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመምህርነት እስከ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንትነት አገልግለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት በነበሩበት ወቅት ለትውልድ የሚሻገሩ አሻራዎችን ተክለው እንዳለፉ ዛሬ ላይ ትምህርት እየሰጡ የሚገኙ የተለያዩ ኮሌጆች ህያው ምስክር መሆናቸውን የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡
በፕሬዘዳንትነት ጊዜያቸው ካበረከቷቸው አስተዋፅኦ መካከል በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔን በማሳለፍ ዓይነስውራን በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ፣ የመጀመርያውን የአካል ጉዳተኞች ተማሪዎች ማዕከል ወይም ( የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ማዕከል) ለብቻው ህንጻ በማሰራት ፕሮፌሰሩ ቀዳሚ ሰው ነበሩ፡፡
በተጨማሪምበፒኤችዲ ደረጃ በርካታ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች እንዲከፈቱ ፣ ሙዚቃ ፣ ቴአትርና ስዕል አንድ ላይ በመሆን ራሳቸውን ችለው እንደ ኮሌጅ በማቋቋም አባተ መኩርያን የመሳሰሉ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ትምህርት ክፍሉ በእግሩ እንዲቆም በነበራቸው ሚና ይጠቀሳሉ፡፡
በ1995ዓም የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ሲረቅም በህገ-መንግስት እና አስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ አባልነት በመካተት የራሳቸውን ሚና ማበርከት የቻሉ ሰው ናቸው፡፡
ከዚህ በላፈም የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ፕሮፌሰር አንድሪያስ በተለያዩ በተለያዩ ዘርፎች በማስተማር በማመከር እና በአመራርነት ከማገልገላቸው ባለፈ ህግ እና ፍልስፍና ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጽሁፎችን ለህትመት በማብቃት ይታወቃሉ፡፡
በወጣትነት ዘመናቸው ለመጀመርያ ጊዜ ሪቻርድ ፓንክረስት በሚያሳትሙት ኢትዮጵያን ኦብሰርቨር መጽሄት ላይ የኢትዮጵያ የመረዳጃ ሀብቶች ስለሆኑት ስለ እድር፤ እቁብ እና ማህበራት ዙርያ ‘’ self-help in Ethiopia “በሚል ርዕሰ አርቲክል በመፃፍ ችለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሞራል እና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች እንዲሁም ስነ-ምግባር ላይ ያተኮሩ የድርሰት ውጤቶችን በበርካታ መንገዶች አሳትመዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ የስራ ተሞክሯቸው በዩኔስኮ የሰብአዊ መብት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሊቀ-መንበር ሆነው የሰሩ ሲሆን ብራውን ፣ ዩሲኤልኤ፣ ዩሲ-በርክሌይ እና ፔንሴልቫንያ በመምህርነት ያገለገሉባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ካተረፉ ዝነኞች ውስጥ አሜሪካዊው የፖለቲካ ፈላስፋ ጆሴፍ ኮን እንዲሁም የሂውማን ራይትስ ዎች ፕሬዘዳንት ኬኔት ሮፍ ከፕሮፌሰሩ ተማሪዎች ውስጥ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከፈላስፋነታቸው ባለፈ በመብት ተሟጋችነት እና በፓንአፍሪካኒስትነት የሚታወቁት ፕሮፌሰሩ በአሜሪካን ሀገር በነበሩበት ወቅት በሰበዓዊ መብቶች ንቅናቄ ላይ እንዲሁም በብላክ ፓንተር ፓርቲ ውስጥም ተሳትፎ እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ከታላላቆቹ ፈላስፎች ውስጥ የፕሌቶ፣የማርክስ እና ሄግልስ አድናቂ ሲሆኑ ከሀገር ውስጥ ምሁራን እነ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ለመንግስቱ ለማ ስራዎች ከፍተኛ ፍቅርና ክብር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
የቅርብ ወዳጆቻቸው ፕሮፌሰሩን ሲገልጿቸው ያመነበትን የሚኖር፣ አንባቢ፣ ተጫዋች ፣ ለልጆች ልዩ ፍቅር የነበራቸው እና ሩህሩህ እንደነበሩ ያነሷቸዋል፡፡
አንድሪያስ ከአብራካቸው ከተገኝው ልጃቸው አሉላ አንድሪያስ በተጨማሪ የአባት ፍቅር እየሰጡ ያሳደጓቸው ሁለት ተጨማሪ ልጆች እንደነበሯቸው የታሪክ መዝገባቸው ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ ቁልፍ የታሪክ ሁነቶች ውስጥ ታዛቢ ብቻ ሳይሆኑ ቁልፍ ተሳታፊም የነበሩት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም አርፈዋል።
የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ነገ እሁድ፣ ጷጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ይፈፀማል።
በዕለቱ ከጠዋቱ 4:00 - 6:00 ሰዓት ባስተማሩበትና በሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ራስ መኰንን አዳራሽ የስንበት ስነ-ስርዓትም የሚከናወን ይሆናል።