ሰራዊቱ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎችን በንቃት ሊከታተል ይገባል ተባለ
ሰላምን ለማደፍረስና የተቻላቸውን ለማድረግ የሚጥሩ አካላትን ሰራዊቱ ከህዝቡ ጋር በመሆን በንቃት ሊከታተል እንደሚገባም ተገልጿል
በአጎራባች ሃገራት የሚታየውን ወቅታዊ ፓለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል ይገባልም ተብሏል
ሰራዊቱ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎችን በንቃት እንዲከታተል ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አሳሰቡ
በሃገር ውስጥ ወቅታዊ የፀጥታ ችግሮች ሳይገደቡ በአጎራባች ሃገራት የሚታየውን ወቅታዊ ፓለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል እንደሚገባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በሰሜን ዕዝ ለከፍተኛ መኮንኖችና ተመጣጣኝ የስታፍ ክፍል ሃላፊዎች ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
"ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ከግጭት ነፃ እንዲሆን አበክራ እየሰራች ትገኛለች" ብለዋል በንግግራቸው፡፡
”የአጎራባች ሃገራት ውስጣዊ የፓለቲካ ችግሮች ለሃገራችን ሰላም ስጋት ሊሆኑ ስለሚችሉ የሰራዊቱ አመራሮች እነዚህንና መሰል እንቅስቃሴዎችን በሳይንሳዊ መንገድ መተንተን ይገባቸዋል“ ሲሉም ነው ያሳሰሰቡት፡፡
“በተለይ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሃብቶቿን ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ጥቅማቸው የተነካባቸው የሚመስላቸው ሃገራት በፕሮጀክት ግንባታዎች ሳይሆን በውስጣችን በሚፈጠሩ የሰላም ችግሮች እንድንጠመድና ግንባታዎች እንዲጓተቱ በእጅ አዙር ሊሰሩ ይችላሉ” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ “የአባይ ተፋሰስ ሃገራት በህዳሴው ግድብ ግንባታና ውሃ አሞላል ዙሪያ እያደረጉት ያለው ድርድር የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ነው” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ሃብቷን ለመጠቀም በምትወስደው አቋም ሰላሟን ለማደፍረስና የተቻላቸውን ለማድረግ የሚጥሩ አካላትን ሰራዊቱ ከህዝቡ ጋር በመሆን በንቃት ሊከታተል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
ተቋማዊ ጉዳዮችን በተጨማሪነት ያነሱት ጄኔራል መኮንኑ ተቋማዊ ሪፎርሙን የሚያስቀጥሉ እና የሰራዊቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በተያዘላቸው እቅድና ፕሮግራም መሠረት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ማብራራታቸውን መከላከያው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡