ታሽገዉ የተቀመጡ የምርጫ ሳጥኖችን በመስረቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ የከተተው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
የምርጫ ቁሳቁሶቹን ለመጠበቅ ያልቻለው ጠባቂም በገንዘብ እንዲቀጣ ተደርጓል
ግለሰቡ ሳጥኖቹን ጥልቀት ካለው ውሃ ጉድጓድ ውስጥ ስለመክተቱ ተነግሯል
በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ አውንት መንዝ ቀበሌ ከሃሙሲት ምርጫ ጣቢያ “ሀ” ታሽገዉ የተቀመጡ የምርጫ ሳጥኖችን በመስረቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ የከተተው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ፡፡
አንለይ በዜ ይሰኛል የተባለለት ግለሰቡ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ/ም ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፡፡
የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤት ተወካዮችን ዝርዝር የያዙ ድምጽ መስጫ ወረቀቶች የተቀመጡባቸውን የምርጫ ቁሳቁስ ሳጥኖች ታሽገው የተቀመጡበትን ስፍራ ሰብሮ በመግባትና ተሸክሞ በመውሰድ ስድስት ሜትር ጥልቀት ካለው የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ስለመክተቱ በምርመራ አጣራሁ ያለው የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የምርመራ መዝገቡ የቀረበለት የወረዳው ዐቃቢ ህግም ግለሰቡ የተጠረጠረበት ወንጀል በማስረጃ የተደገፈ ሆኖ ስላገኘዉ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 157/3/መ የተመለከተዉን ተላልፏል ሲል ክስ መስርቶበታል፡፡
የቀረበለትን ክስ ያደመጠው የወረዳው ፍርድ ቤትም ተከሳሹ የተጠረጠረበትን ወንጀል የፈጸመ መሆኑን በማመኑ ተከሳሹንና መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል በሚል በ3 ወራት እስር እንዲቀጣ ዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ የምርጫ ቁሳቁሶችን እንዲጠብቅ ተመድቦ የስራ ኃላፊነቱን ያልተወጣዉ ግለሰብ በ1 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑንም የዞኑ ዐቃቤ ሕግ መምሪያ አስታውቋል፡፡
መምሪያው የተጓደሉ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ ተሟልተው ምርጫው እንደማንኛው ምርጫ ጣቢያ በተያዘለት ጊዜ ተካሂዶ መጠናቀቁንም ነው ያስታወቀው፡፡