ታሪካዊ የተባለው የመካከለኛው ምስራቅ ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?
“ሁሉም ወገን አሸናፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በሚያስችል እና ከጥርጣሬ በጸዳ መልኩ የተፈጸመ ስምምነት ነው”
በዩኤኢ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው ስምምነት የመካከለኛው ምስራቅን የወደፊት የግንኙነት እጣ ፋንታ እንደሚወስን ይጠበቃል-ተንታኞች
የዩኤኢ እና እስራኤል ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል ከሰሞኑ ታሪካዊ ከተባለ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ስምምነቱ የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከማስቻል ባሻገር በተለያዩ መስኮች እንደሚተባበሩ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡
ተቀዛቅዞ አመታትን የዘለቀው የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲነቃቃና ኤምባሲዎቻቸውን እንዲከፍቱ ለማድረግም ያስችላል፡፡
ስምምነቱን ታሳቢ በማድረግም ከትናንት በፊት ይፋዊ የስልክ ግንኙነቶችን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የሃገራቱ ባለስልጣናት በቅርቡ ተገናኝተው ስምምነቱን እንደሚፈርሙም ይጠበቃል፡፡
ለመሆኑ ስምምነቱ ምን አንድምታ አለው ምንስ ጥቅምን ሊያስገኝ ይችላል?
ስምምነቱ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣይ እጣፋንታ ላይ አዲስ አቅጣጫን ሊያመላክት ብሩህ ሊባል የሚችል ትልቅ ተስፋን ሊያጭር የሚችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡
እስራኤል ከ25 ዓመታት በኋላ ከአረብ ሃገር ጋር የፈረመችው የመጀመሪያው ስምምነት ነው ያለው እየሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ በቀጣናው ቀጣይ የሰላም እጣፋንታ ላይ ተስፋን የፈነጠቀ እንደሆነም ዘግቧል፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰሩ አህመድ ዘካሪያም መስማማቱ ለቀጣናው ሰላም ጥሩ እንደሆነ እና አበርክቶው ወደፊት እንደሚታይም ገልጸዋል፡፡
ስለ ስምምነቱ መልካምነት የሚናገረው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛው ስላባት ማናዬም ይህንኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ይሰነዝራል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የዲፕሎማሲ እና የጂኦ ፖለቲካ እንዲሁም በዓባይ የውሃ ጉዳዮች ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎችና በሚያቀርባቸው ትንታኔዎችም የሚታወቀው ስላባት የሰላም ስምምነቱ “ዩኤኢ ከሌሎች ሃገራት በተለየ ከመጋረጃ ጀርባ ወጥታ ፊት ለፊት ያደረገችው ነው” ይላል፡፡
“ይሄ ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መንገድ ሁሉም ወገን አሸናፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በሚያስችል እና ከጥርጣሬ በጸዳ መልኩ የተፈጸመ ነው” ሲልም ነው ‘የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ’መጽሃፍ ደራሲው ጋዜጠኛ የሚናገረው፡፡
“ከአሁን በፊት ግብጽ እና ዮርዳኖስን ሲወቅሱ የነበሩ ናቸው አሁን ዩኤኢን ሊወቅሱ የሚፈልጉት ይህ ግን እንደሚሉት ሳይሆን የዩኤኢ በፍጥነት ወደፊት መምጣት እና ዓለም አቀፍ ተሰሚነትን ማግኘት ስለሚያንገበግባቸው ነው” ሲልም ያስቀምጣል፡፡
ዩኤኢ ከሌሎቹ የአረብ ሃገራት በተለየ ሊበራል ነች ሲልም ይገልጻል ሃገሪቱ ለአዳዲስ የዴሞክራሲ እና የምጣኔ ሃብት እንዲሁም ሌሎች እሳቤዎች ያላትን ቀናዒነት ለማመላከት፡፡
ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?
ስምምነቱ በቀጥታ ኢትዮጵያን የሚመለከት ወይም ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊኖረው የማይችል ቢሆንም ተዘዋዋሪ አበርክቶ ሊኖረው እንደሚችል ቀደም ሲል የተጠቀሱት ምሁራን አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ሁለቱም ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት አላቸው የሚለው ጋዜጠኛ ስለባት የቀጣናው ሰላም መሆን ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት፣ ለጀመረቻቸው የልማት ተግባራት ስኬት እንደሚጠቅማት ይገልጻል፡፡
ይህ “በተለይ ከውጭ ቀጥታ የኢንቨስትመንት ፍሰቶች ማደግ ጋር ይያያዛል”ም ነው የሚለው፡፡
ለዚህም የዩኤኢ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ዘርፎች እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ ማደጉን በማሳያነት ያስቀምጣል፡፡
ከሁለቱም ሃገራት ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ገለልተኛ አካሄድን እንደምትከተል የሚናገሩት ፕሮፌሰር አህመድም ስምምነቱ በቀጥታ ኢትዮጵያን የሚመለከት ባይሆንም ሊያመጣ የሚችለው ችግር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡
“እኛ ‘ኒውትራል’ ሆነን ከሁሉም ጋር ግንኙነት ያለን ነን ከሁሉምጋር በሰላም መኖር እና መተባበር እስከቻልን ድረስ ሊጠቅመን እንጂ ሊጎዳን የሚችል አይመስለኝም” ሲሉም ያስቀምጣሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
“የመካከለኛ ምስራቅ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የቀረበ በመሆኑ ተሻጋሪ ሊባል የሚችል ‘ስፒል ኦቨር ኢፌክት’ አለው” የሚሉት በኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሻሜቦ ፊጣሞ “ስምምነቱ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ ያስችላል” ይላሉ፡፡
“ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በባህረ ሰላጤው አካባቢ ያለው ሰላም እንዲጠበቅ ትፈልጋለች” ያሉም ሲሆን በቀጥታም ባይሆን ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረውና አብሮ ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
በቀጣናው ሰላም መሆን ኢትዮጵያ እንደምትጠቀምም ነው የተናገሩት፡፡