የፖምፔዮ ጉብኝት በዩኤኢ እና እስራኤል የሰላም ስምምነት ላይ የሚያተኩር ነው ተብሏል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ እስራኤል ገቡ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በመካከለኛው ምስራቅ ለሳምንት ያህል የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬ በእስራኤል ጀምረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጉብኝት ዓላማ የእስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሰላም ስምምነት ሲሆን ሌሎች የአረብ ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ መምከር ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሞርጋን ኦርታጉስ እንዳሉት ማይክ ፖምፔዮ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በኢየሩሳሌም በሚኖራቸው ቆይታ ከኢራን ጋር በየሚገናኙ ቀጣናዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ፡፡ እስራኤል በቀጣናው ያላትን ግንኙነት እና ትብብር በማጠናከር የአሜሪካ እና የእስራኤልን ጥቅም ማስጠበቅ በምትችልበት ጉዳይ ላይም እንደሚነጋገሩ ቃል አቀባይዋ ገልጸዋል፡፡
ቀጥሎ ወደ ሱዳን በማቅናት ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን እና ከሉዓላዊው የምክር ቤት ሃላፊው ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በሲቪል ለሚመራው የሽግግር መንግስት አሜሪካ በምታደርገው ድጋፍ ዙሪያ ይመክራሉ፡፡ “የሱዳን እና የእስራኤል ግንኙነትን የበለጠ ለማጎልበት አሜሪከ ድጋፍ እንደምታደርግም ይገልጻሉ” ነው ያሉት ሞርጋን ኦርታጉስ፡፡
ሱዳን ሽብርተኝነት ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ዉስጥ ስሟ እንዲሰረዝ አሜሪካን በመወትወት ላይ የምትገኝ ሲሆን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ለዚህ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
ከሱዳን በመቀጠል ፖምፔዮ ወደ ባህሬን ተጉዘው ከባህሬን ዘውዳዊ ልዑል ሰልማን ቢን ሀማድ አል ካሊፋ ጋር ይወያያሉ፡፡
ከባህሬን መልስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚያቀኑት ፖምፔዮ ጉብኝታቸውን ቅዳሜ እለት እንደሚያጠናቅቁ ዘናሽናል ዘግቧል፡፡
እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባለፈው ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በደረሱት የሰላም ስምምነት የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለመጀመር ተስማምተዋል፡፡ ይህ ስምምነት እስራኤል በቁጥጥሯ ስር የሚገኘውን የዌስት ባንክ ክፍል የመጠቅለል እቅዷን የገታ ነው፡፡ ዩኤኢ ለመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማሲ የስትራቴጂ ለውጥ አድርጋ የወሰደችው ይህ ከእስራኤል ጋር የተደረሰው ስምምነት በአብዛኛው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ተችሮታል፡፡