የአውሮፓ ህብረት ከአሜሪካ ጦር ጥገኝነት የሚያላቅቀውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዲያቋቁም ሃሳብ ቀረበ
የመከላከያ ኃይሉ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ሺ አባላት ኖረውት ሊቋቋም እንደሚችልም ነው የተነገረው
ህብረቱ፤ “አሁናዊ የአፍጋኒስታን ሁኔታ የአባል ሃገራቱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል ኃይል እንደሚያስፈልግ በውል ያመላከተ ነው” ብሏል
የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መንግስታት የጋራ ጦር እንዲያቋቁሙ የህብረቱ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጠየቁ፡፡
ባለስልጣናቱ ህብረቱ ፈጥኖ በመድረስ የአባል ሃገራቱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የመከላከያ ኃይል ማቋቋም ስለማስፈልጉ ሰሞነኛው የአፍጋኒስታን ሁኔታ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የህብረቱ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦሬል ኢ- መደበኛ በሆነ ስብሰባ ከህብረቱ ወታደራዊ ኮሚቴ ጋር በስሎቬኒያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ዲፕሎማት እና የኮሚቴው ኃላፊ ከአባል ሃገራቱ ውጭ ሊነሱ ለሚችሉ ግጭቶች ፈጥኖ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል የመከላከያ ኃይል መቋቋም ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ኃይሉ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ሺ አባላት ኖረውት ሊቋቋም እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
ይህ መሆኑ ህብረቱ በአሜሪካ ላይ ካለው ወታደራዊ ጥገኝነት ለመላቀቅ እንደሚያስችለውም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
የወታደራዊ ኮሚቴው ሊቀመንበር ጄ/ል ክላውዲዮ ግራዚያኖ “በአፍጋኒስታን፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሳህል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ከማቋቋም ጀምሮ የህብረቱን ዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂክ የአጋርነት ፍላጎት ለማሳየት ጊዜው አሁን መሆኑን አመላካች ነው” ብለዋል፡፡
ቦሬል በበኩላቸው አውሮፓን ሊከላከል እና ፍላጎቶቿን ሊጠብቅ የሚችል “ጠንካራ የጋራ ኃይል” እንደሚስፈልግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ እየሆነ መጥቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃሳቡን የተመለከተ የመጨረሻ ዕቅድ በመጪው ጥቅምት ወይ ህዳር ለህብረቱ ምክር ቤት እንደሚያቀርቡም ነው ቦሬል የተናገሩት፡፡
ህብረቱ እንዲህ ዐይነት ኃይልን ለማቋቋም ካሰበ 10 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ውጥኑ 1 ሺ 500 አባላት ያሉትንና እምብዛም ያልተጠቀመበትን አንድ ሻለቃ ጦር ከማቋቋም አልዘለለም፡፡
ይህ ደግሞ አባል ሃገራቱ በገንዘብ እና ሰው ኃይል መዋጮ ላይ ባለመስማማታቸው የሆነ ነው፡፡