አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ቅርጽ ፕሬዝዳንታዊ አይሆንም- ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)
ሚኒስትሩ በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያገኙት ውጤት ”በቂ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ለማንጸባረቅ በሚያስችል መልኩ በአዲሱ መንግስት እንደሚወከሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት መሰረትፓርላመንታዊ ሆኖ እንደሚቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ከሶስት ሳምንታት በፊት ባደረጉት ቆይታ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት አሁን በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፓርላመንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ የመንግስት ስርዓት ልትቀይር ትችላልች የሚሉ መረጃዎች ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡
- በምርጫው ብልጽግና ከፍተኛ ድምጽ ሲያገኝ 3 የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ ወንበር አግኝተዋል
- ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖራው ያደርጋል-ጠ/ሚ ዐቢይ
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑ የመንግስት መሪዎች የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት በመሆናቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ፓርላመንታዊ የነበረው የመንግስት ስርዓት ፕሬዝዳንታዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ የአንድን ሀገር ስርዓት በአንድ ጊዜ ተነስቶ ከፓርላመንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ መቀየር እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ሰፊ ስራ እና ውይይት እንደሚጠይቅ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከምንም በላይ ደግሞ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ሕገ መንግስታዊ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ቢቂላ (ዶ/ር )፤ የመንግስትን ስርዓት ፕሬዝዳንታዊ ወይም ፓርላመንታዊ የማድረግ ሃሳብ የሕዝብ በመሆኑ ውይይት እንደሚጠይቅ ያነሱ ሲሆን፤ በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ መታየት ያለባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉና ሀገርን የማሻሻሉ ስራ ቀን የሚቆረጥለት ባለመሆኑ ወደፊት ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ከሁሉም፤ በሁሉም፤ ለሁሉም መሆን አለበት የሚል መርህ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ኢትጵያውያ የኢትዮጵያውያን ናት የሚለውን በተግባር መሬት ላይ ማንጸባረቅ መቻል እንደሚገባ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ በተደረገው ምርጫ የተወሰነ ድምጽ ያገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖራቸው ቀደም ካለው ታሪክ አንጻር መልካም ጅምር መሆኑን ያነሱ ሲሆን ውጠቱ ግን “በቂ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት እየተሻሻለ፤ ዘመናዊ እየሆና እየጠነከረ ሲሄድ ከዚህ በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምጽ አግኝተው የሕዝባቸውን ፍላጎት በፓርላማ እና በክልል ም/ቤቶች ማንጸባረቅ መቻል እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን በምርጫ ለተገኘው የድምጽ ውጤት ምን ማድረግ አለብን በሚል በተለያየ አጋጣሚ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትም ሆኑ ሌሎች አመራሮች እንደገለጹት፤ የሚመሰረተው መንግስት አካታች እንደሚሆን ቢቂላ (ዶ/ር) ተናረዋል፡፡
የሚመሰረተው መንግስት በተቻለ መጠን በሁሉም የመንግስት እርከኖች እና መዋቅሮች ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በግለሰብ አመራር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ሃሳባቸውን ለማንጸባረቅ በሚያስችል ሁኔታ የሚወከሉበት፤ የሚሳተፉበት እና ድምጽ የሚያሰሙበት እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው ተብሏል፡፡
ይህንን ለማድረግም “የተለያዩ አሰራሮችን እና አማራጮችን ስንመለከት ነበር” ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር) በትክክልም የሚመሰረተው መንግስት በተቻለ መጠን እንደድሮው አንድ ፓርቲ ወይም ሁለት ፓርቲ ብቻ ዝም ብሎ ድምጹን የሚያሰማበት አይሆንም ተብሏል፡፡
የተለያዩ ፓርቲዎች ወኪሎች ሃሳባቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት፤ በተለያዩ የመንግስት እርከኖች ውስጥ የሚሳተፉበት እና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተስፋ የሚሰጡ ስራዎችን የሚሰሩበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ሰኔ 16-2013 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፤ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና አብላጫ ድምጽ ማግኘጹንና ሌሎች ሶስት ተቀዋሚ ፖርቲዎች የፓርላ መቀመጫ ማሸነፋቸውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ጠቅላላ ምርጫው በተለያየ ምክንያት በሁሉም የምርጫ ክልሎች መካሄድ ባይችልም፣ ምርጫ ቦርድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ መገኘቱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት አስታውቋል፡፡