“ድርድርን እንደ ማደናገሪያ ስትራቴጂ ከሚጠቀም አሸባሪ ቡድን ጋር መነጋገር ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ብለን አናምንም”- ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ
ህወሓት ድርድርን ለማደናገሪያነት ለመጠቀም እንደሚፈልግ እና ይህንንም በሰነድ አስደግፎ ማዘጋጀቱን መንግስት አስታውቋል
ህወሓት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የፖለቲካና ወታደራዊ ኃይል ሆኖ መቀጠል እንዳይችል ተደርጎ እንዲደመሰስ አቋም ተይዟል ብለዋል
በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሃት ድርድርን ለማደናገሪያነት ለመጠቀም እንደሚፈልግ እና ይህንንም በሰነድ አስደግፎ ማዘጋጀቱን መንግስት አስታወቀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ድርድርን እንደ ማደናገሪያ ስትራቴጂ ከሚጠቀም አሸባሪ ቡድን ጋር መነጋገር ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ብለን አናምንም” ብለዋል።
ህወሓት መደራደርን ለማደናገሪያነት እንጅ ለእውነተኛ ሰላም የሚጠቀም እንዳልሆነ ያነሱት ዶ/ር ቢቂላ ፤ ቡድኑ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ የመፍታት ስነልቦና፣ ብቃት እና ልምድ እንደሌለውም ተናግረዋል።
ህወሃት ድርድርን የሚጠቀመው “ትንፋሽ አግኝቶ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማሳሳት፤ ጊዜ አግኝቶ ኃይል ለማከማቸት እና ሴራውን ለማስቀጠል እንጅ ቁጭ ብሎ ተደራድሮ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በላይ ሰቆቃ አይገባውም በሚል አስቦ አይደለም” ብለዋል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት፤ ህወሓት የሀገሪቱን ሰላም ማወክ እስከማይችልበት ጊዜ ድረስ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የፖለቲካና ወታደራዊ ኃይል ሆኖ መቀጠል እንዳይችል ተደርጎ እንዲደመሰስ አቋም መያዙንም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ይህንን ውሳኔ የወሰነው በአንድ ወገን ሰላም ስለተፈለገ ብቻ ህወሓት ወደ ሰላም ይመጣል ብሎ ስለማያምን መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ቢቂላ፤ በዚህ የተነሳም “ኢትዮጵያውያን የትም፣ መቼም፣ በምንም ዘምተን ይህንን ቡድን ከምድረ ገጽ ማጥፋት አለብን ብለው ተነስተዋል“ ብለዋል።
በታሪክ አጋጣሚ “በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የመጣ አውዳሚ ኃይል ወደተመኘበት መቃብር መመለስ አለብን ብለን እየተረባረብን” ሲሉም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ዶ/ር ቢቂላ፤ በቁጥጥር ስር ሳይውሉ የቀሩ ከፍተኛ የህወሃት አመራሮች በፍርድ አደባባይ የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህም ሕዝቡ በሚችለው ሁሉ ድጋፉን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊ መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ እንደምትፈልግ ያነሱት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ ህወሃት ግን ኢትዮጵያን የማፍረሻ ግብ አድርጎ በወረቀት ያሰፈረው መደራደር እና መነጋገርን እንደማደናገሪያነት መጠቀም መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሰሞኑ የዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ ሚሽን ኃላፊ፤ መጋዘኖች መዘረፋቸውን ማመናቸው ግማሽ ዕውነትን ለዓለም እንዳሳወቁ እንደሚቆጠር የገለጹት ዶ/ር ቢቂላ፤ ህወሃት “አሸባሪ” መሆኑን በተግባር እያሳየ አሜሪካ ግን ይህንን አለመገንዘቧ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ የዩኤስኤይድ መጋዘኖች መዘረፋቸውን እንደገለጸችው ሁሉ ፤ በደብረታቦር በንጹሃን ላይ ሚሳኤል ተተኩሶ ያንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን፤ ጨጨሆ መድሃኒ ዓለም ላይ መድፍ ተተኩሶ ድሆች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት የእምነት ተቋም መፍረሱን፤ ምንም የሌላቸው ድሆች የሚታከሙበት የንፋስ መውጫ ሆስፒታል መዘረፉን በግልጽ መናገርና ማውገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ህወሓት በደብረታቦር በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው የተባሉ 5 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
ህወሃት ከነፋስ መውጫ ሆስፒታል መኪና አቁሞ መድሃቱን ሲጭን፤ አፋር ላይ በህጻናት ላይ ከባድ መሳሪያ ሲተኮስና ሲገደሉ፤ የእንስሳት መንጋ ላይ ተኩስ ተከፍቶ የድሃ እንስሳት ሲያልቁ አሜሪካ ዝም ማለት እንዳልነበረባትም ዶ/ር ቢቂላ ገልጸዋል።
ከሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያንና ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ችግሮችን ለመፍታት የቀድሞውን የናይጀሪያ ፕሬዘዳንት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡ነገርግን ህወሃት የአፍሪካ ህብረትን ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡