ፓርቲው “ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ” ይዘው መምጣታቸውን አስታውቋል
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴን ምስል አካቶ “አላልንም ወይ ያሠኛል! ኢትዮጵያን አትንኩ!” ሲል በይፋዊ የማህበራዊ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ አሜሪካ ኢትዮጵያን የመበታተን እቅድ አላት ብሏል።
ብልጽግና በጽሁፉ ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብጽና ሱዳን ጉብኝት ያደረጉት ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ይዘው መጥተው ነበር ብሏል።
“ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮውን ለማሳካት የነደፈውን አቀራረብ ያልተረዳን አላዋቂዎች አድርጎን ከሆነ የዋሁ እሱ ራሱና አጋፋሪዎቹ ናቸው” ሲልም ያትታል ጽሁፉ።
“ኢትዮጵያን የመበተን ሴራ ጉዳይ ለእኛ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም” የሚልም ሲሆን የአባቶቻችን ልጆች የእናቶቻችን ፍሬዎች ነን ሲልም ያክላል።
ጉዳዩ የአንድ ፓርቲ ወይም የመንግስት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ብሔር ብሔረሰቦች ኢትዮጵያዊውያን የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ይገልጻል።
“ኢትዮጵያዊያን በጊዜያዊ የውስጥ ችግሮቻችን ሳንያዝ ጣሊያንን ባንበረከክንበት ያ የሀገር ፍቅር ክንዳችን ዛሬም ሳንለያይ የውጭ ኃይላትን ሴራ በህብረትና በአንድነት መመከት ይቻላል” ሲልም ነው በፓርቲው ይፋዊ የማህበራዊ ገጽ የሰፈረው ጽሁፍ የሚነበበው።
“እኔ እያለሁና እያየሁ ጠላቶቻችን ሀገሬን በላዬ አያፈርሱም እኔም የአባቶቼ ልጅ ነኝ” የሚል ትውልድ ዛሬም አለ ብሏል የሚለው ብልጽግና ሀገር ሲኖረን የውስጥ ችግሮችን በመካከር ማረም እንደሚቻል በመጠቆም፡፡