ኢትዮ ቴሌኮም ካለበት ዕዳ 67 በመቶውን መክፈሉን አስታወቀ
ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስጀመሩት “ቴሌ ብር” የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) ገንዘብ ማስተላለፊያ እና መገበያያ መተግበሪያ ከፍተኛ ግብይት እየተደረገበት መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ የቀጣይ ዓመት ( 2014 ዓ.ም) ዕቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡
“ቴሌ ብር” ስራ ከጀመረ 100ኛ ቀኑ ማስቆጠሩን በዕቅዱ ይፋ ማድረጊያ መድረክ የገለጹት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አሁን ላይ 3 ሺ 643 የንግድ ተቋማት በቴሌ ብር ግብይት እያካሄዱ መሆኑ የገለጹ ሲሆን ስድስት የኢትዮጵያ ባንኮችም አገልግሎታቸውን ከቴሌ ብር ጋር ማስተሳሰራቸውን ተናግረዋል፡፡
ቴሌ ብር ጥሬ ገንዘብ ወይም ቼክ መያዝን የሚያስቀር “ዲጂታል” የክፍያ እና የግብይት አገልግሎት ዘዴ ነው፡፡ የአግልግሎቱ ፈላጊዎች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዥ እንዲፈፅሙ ያስችላል፡፡ እስካሁንም አገልግሎቱን ለመስጠት በህጋዊነት የተመዘገቡ 18 ሺ 656 ወኪሎች መኖራቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ ለሁለት የውጭ ድርጅቶች ፈቃድ እንደሚሰጥ መንግስት ከአሁን ቀደም አስታውቋል፡፡ ጨረታ አሸንፈው ስራ ለመጀመር በሚያስችላቸው የዝግጅት ሂደት ላይ ያሉም አሉ፡፡ ሆኖም ድርጅቶቹ በቴሌ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ አይደሉም፡፡ ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ አገልግሎቱን በቴሌኮም በኩል ለመስጠት እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በማሰብ የተደረገ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በአንድ ዓመት ውስጥ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተው የነበሩ ኩባንያዎች ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለመንግስት እንክፈል ብለው የነበረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን ኢትዮ ቴሌኮም ይህን በአጭር ጊዜ ያካክሰዋል የሚል እምነት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህም አንድ ዓመት ተሰጥቶታል፡፡ ዕድሉን ለመጠቀም ካልቻለ ሌሎች እንዲገቡ እንደሚፈቀድና ለዚህም ራሱን እንዲያዘጋጅም ነው ጠ/ሚ ዐቢይ ያስታወቁት፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በ 2013 ዓ.ም ያገኘው ገቢ 56 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሲሆን በ 2014 ዓ.ም ደግሞ 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የነበረበት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 56 ቢሊዮን ዶላሩን ወይም 67 በመቶውን ከፍሏል፡፡ ቀሪውን 881 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ እ.አ.አ እስከ 2029 መክፈል እንደሚከፍል ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት፡፡
ፍሬህይወት ኩባንያው በቀጣይ አዳዲስ አገልግሎቶችን እንደሚጀምር እና ለደንበኞቹ የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቸው ሃምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በተጀመረው አዲስ የበጀት ዓመት የደንበኞቹን ብዛት 64 ሚሊዮን ለማድረስ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡