የግሉ ዘርፍ በኃይል ማምረትና አቅርቦት ዘርፍ እንዲሳተፍ የአፍሪካ መሪዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
የግሉ ዘርፍ በኃይል ማምረትና አቅርቦት ዘርፍ እንዲሳተፍ የአፍሪካ መሪዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
በአፍሪካ ከሚኖረው ከ1.2 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ኤሌክትሪክ እንደማያገኝ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ሰሜን አፍሪካ የተሻለ የኃይል አቅርቦት ያለው ሲሆን ከሰሃራ በታች ያሉት አፍሪካውያን ግን ከ30 በመቶ በታች ነው ኤሌክትሪክ የሚያገኙት፡፡ይህ ግን ደቡብ አፍሪካን አያካትትም ምክንያቱም ደቡብ አፍሪካ 86 በመቶ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል፡፡ በጥቅሉ ግን በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ ዜጎች ቁጥር በርካታ ሲሆን ገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ የበለጠ ለዚህ ተጋላጭ ናቸው፡፡
የአፍሪካን የኃይል ዘርፍ የተመለከተ ውይይትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡
ይህ ውይይት 3ኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ምክክር ሲሆን የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንጌ እና የሞዛምቢክ ጠቅላይ ሚኒስትር ካርሎስ አጎስቲንሆ ሮዛሪዮ የአፍሪካን የኃይል ዘርፍ የተመለከተ ውይይት ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና የኩባንያ ተወካዮች ጋር አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባው ውይይት በአፍሪካ የኃይል ዘርፍ ላይ ያተኮረ ሲሆን በቀጣይ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የኃይል ዘርፉ ላይ መስራት እደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡አሁን ለይ በአህጉሩ ከ570 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፡፡ ይሁንና በአፍሪካ በጂኦተርማል፣በጸሃይና በእንፋሎት ኃይልን ማመንጨት ይቻላል፡፡
ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ በተቀመጠው መሰረትም በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በቀጣይ 5 አመታት በአፍሪካ 10ሺ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ስራ ለመስራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡በዚህ ውስጥ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ለማድረግ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸውም የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙት 570 ሚሊዮን ዜጎች እስከ በ2030 ኤሌክትሪክ ያገኛሉ የሚል ዕቅድ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግል ባለሃብቱ ወደ ኃይል ልማት ዘርፍ መግባት እንዳበት ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚያነሱት።
ለመሆኑ ከ10 ዓመት በኋላ ሁሉም የአፍሪካ ዜጎች ኤሌክትሪክ ያገኛሉን?
በተባሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ኦፊሰርና የኃይልና መሰረተ ልማት ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ኃይሉ ሁሉም አፍሪካውያን ኤሌክትሪክ ያገኙ ዘንድ ከመንግስት በተጨማሪም የግል ኩባንያዎች መሳተፍ አለባቸው ብለዋል፡፡ እስካሁን በአፍሪካ የግል ዘርፉ በኃይል ዘርፍ ላይ በሚፈለገው ልክ አለመሰማራቱን የሚያነሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ይህ ግን ሊያበቃ ይገባል ይላሉ፡፡በመሆኑም ሃገራት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከግል ባለሃብቶች ጋር መስራት አለባቸው ነው የሚሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም ባለሃብቶች በኃይል ልማት ዘርፍ እንዳይሰማሩ የሚያደርጉ ህጎችን ማሻሻል፣ አካባቢን ለስራ ምቹ ማድረግና በጋራ መስራት ውጤቱን ለማየት አስፈላጊነቱን ያነሳሉ፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋጋዋ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር እንዲመጣ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የኃይል እጥረት መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሃገራቸው የግል ባለሀብቶች በኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሙሉ ለሙሉ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቀዋል፡፡በዘርፉ ለመሰማራትና ኃይል ለማመንጨት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች በዚምባብዌ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት ቢሰማሩ ጥቅሙ የጋራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የግል ባለሃብቶች በሶላር፣ በጂኦተርማልና በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ዘርፍ ቢሰማሩ ትርፋማ ከመሆንም ባለፈ በአፍሪካ ዘመናዊ ኢኮኖሚ እንዲኖር ለማድረግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል፡፡ የሞዛምቢክ ጠቅላይ ሚኒስትር ካርሎስ አጎስቲንሆ ሮዛሪዮ ልክ እንደ ምናንጋግዋ ሁሉ ሃገራቸው ለግል ባለሃብቶች የምትመች መሆኗን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ እዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በኃይል ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ካሉ አብረው ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የፓሲፊክ ኢንቨስትመንት ማኔጀመንት ኩባንያ ስትራቴጅስት ስኮት ማተር ሃገራት ባለሃብቶችን ከመጥራት ባለፈ ህጎቻቸውን ምቹ ማድረግ፣ ለችግሮችና ኪሳራዎች ዋስትና መግባትና ሌሎች ለቢዝነስ የሚያስፈልጉትን ሁሉ ማሟላት አለባቸው ብለዋል፡፡
እኤአበ2030 ሁሉንም በአፍሪካ የሚኖሩ ሰዎች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጄንሲ እንደገመተው ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ለኃይል ዘርፍ ከ2017 እስከ 2030 ለዘርፍ ከሚያስፈልገው 445 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን ፈሰስ የተደረገው 35 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ይህ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ሰባተኛ ተራ ቁጥር ላይ የተቀመጠውን ሁሉም ዜጎች ኤሌክትሪክ ያገኛሉ የሚለውን እንዳይሳካ ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡
ኢትዮጵያ ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር በገባችው ቃል መሰረት በዚህ ውስጥ የኃይል ዘርፉ አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የዳዋ ገናሌ ቁጥር 3 የኃይል ማመንጫ ሲመረቅ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከመንግስት ጋር ሆነው እንዲገነቡ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይህ ሃሳብ ለግል ዘርፉ ከሚሰጠው ትኩረት ባለፈም የልማት ግቦችን ለማሳካት ይረዳል ብለው ያምናሉ፡፡ አፍሪካ ከ10 ዓመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከኩራዝ ወደ ኤሌክትሪክ ትሸጋገራለች የሚለውን ዕቅድ ዓለም ሁሉ እየጠበቀው ነው፡፡