አደጋው በ5 ተሽከርካሪዎች ግጭት የደረሰ ነው
ዛሬ ማለዳ ጅቡቲ መንገድ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አለፈ
ከድሬዳዋ ወደጂቡቲ በሚወስደው መንገድ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ላፍዴሬ በሚባል ስፍራ ከማለዳው 11:00 አካባቢ በደረሰ የመኪና አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አልፏል።
አደጋው የደረሰው በ3 መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ እና በ2 ትራከር ከባድ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ግጭት ሲሆን በ5 ሰዎች ላይ ከባድ በ7 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ከፍተኛ የንብረት ጉዳትንም እንዳስከተለ ነው ድሬዳዋ መገናኛ ብዙሃን የዘገበው።
አደጋው በግምት ከንጋቱ 10 ሰአት አካባቢ የደረሰ ነው ያለው የገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ የሰሌዳ ቁጥሩ 53697 ኢት የሆነ ኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነ መኪና ከደወሌ መስመር ወደ ድሬደዋ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ በተቃራኒ አቅጣጫ ከድሬዳዋ ወደ ደወሌ በመጓዝ ላይ ከነበሩ ሶስት የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስና አንድ ባለ ተሳቢ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ጋር መጋጨቱን አስታውቋል፡፡
በፍጥነት ሲጓዝ የነበረው እና ኮንትሮባንድ የጫነው ተሽከርካሪ በሚኒባሱና በጭነት መኪናው ላይ ባደረሰው ከባድ የትራፊክ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷልም ነው ያለው። በዚህም 16 ዜጎች ሲሞቱ 12 ደግሞ ከባድ ጉዳት አስተናግደዋል።
አሰቃቂውን ጉዳት ያደረሰውና ኮንትሮባንድ የጫነው ተሽከርካሪም በፍጥነት በመጓዝ ለማምለጥ በመሞከር ላይ ሳለ ተገልብጧል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚካዔል እንዳለ ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ወደ ድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል መጥተው ተጨማሪ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ከሟቾቹ መካከል የ12ቱ አስከሬን ወደ ሪፈራል ሆስፒታሉ መጥቷል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረ አንድ ሰው ህክምና ላይ ሳለ መሞቱን ገልጸዋል፡፡
የቀሪዎቹ ሟቾች አስከሬን ወደ ሪፈራል ሆስፒታሉ ያልመጣው ምናልባትም ቤተሰብ ወደ ቤት አልያም ወደ ሌሎች የህክምና ተቋማት በመውሰዱ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው 3 ሰዎች ቀዶ ጥገና ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን ሌሎች 5 ሰዎች ታክመው ከሆስፒታሉ ወጥተዋል፡፡
የአደጋው መንስዔ ገና ሊጣራ የሚችል ቢሆንም ቅድሚያ አለመስጠት እና የፍጥነት ችግር ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ መናገሩን አስታውቀዋል፡፡