ቁልፍ የስልጣን አጋሮቻቸውን ጭምር ያጡት፤ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል
የጤና እና ሌሎችም ሚኒስትሮቻቸው ስልጣን ለቀዋል
ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው ነው
ቁልፍ የስልጣን አጋሮቻቸውን ጭምር ያጡት፤ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ተነገረ፡፡
ጆንሰን ስልጣን ይልቀቁ የሚል የበረታ ጫና ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጭምር እየተደረገባቸው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሁን ቀደም ፈጽመዋቸዋል ከተባሉ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ጋር በተያያዘ ስልጣን እንዲለቁ ጫናዎች ሲደረጉ ነበረ፡፡
መተማመኛ ተስኖናል ያሉ ባለስልጣናት መበርከታቸውን ተከትሎ በቅርቡ በስልጣን ይቀጥሉ በሚለው ላይ በምክር ቤት አባላት የመተማመኛ ድምጽ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ 45 በመቶ ያህል የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን ባልሰጡበት በመተማመኛ ድምጹም ጆንሰን ከስልጣን ከመሰናበት ለጥቂት መትረፋቸውም ይታወሳል፡፡
ሆኖም ከሚመሩት ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮቻቸው ጭምር የሚቀርበው ጥያቄ አሁንም በርትቶ ቀጥሏል፡፡ ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ብቻም ሳይሆኑ አብረን ለመቀጠል አንችልም በሚል በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን የሚለቁ የካቢኔ አባላቶችም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ለዚህም ዛሬ ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ ያሳወቁትን የጤና ሚኒስትሩን ሪሺ ሱናክን ጨምሮ የቀድሞው የጤና ሚኒስትር ጃቪድ ሳቪድ እንዲሁም ሌሎች 22 ባለስልጣናት ማሳያ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም በግምጃ ቤት ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ቻንሰለር ሪሺ ሱናክ በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን ከለቀቁ ከፍተኛ የሃገሪቱ መንግስትና የወግ አጥባቂ ፓርቲ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈጽሟቸውን "ቅሌቶች" ለመታገስ አልቻልንም ያሉት ጃቪድ ሳቪድ "ከበቃ በቃ ነው" ሲሉ ተናግረዋል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግድፈቶች በየቀኑ መሸሸግና መዋሸት እንደሰለቻቸው በመጠቆም፡፡ የቀድሞው ጋዜጠኛ ስልጣን እንዲለቁም ነው ባለስልጣናቱ በይፋ የጠየቁት፡፡
ራሳቸውን የሚያገሉ ባለስልጣናትን በአዳዲስ ሰዎች ለመተካት ጥረት በማድረግ ላይ ያሉት ጆንሰን በበኩላቸው ስልጣን እንዲለቁ ግፊት በማድረግ ላይ ያሉ አካላት ቀጣዩን ምርጫ አሸንፈው በስልጣን ይቀጥላሉ በሚል የሰጉ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሊዝ ትረስ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤን ዋላስ እና ሌሎችም ባለስልጣናት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡትን ጆንሰንን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው እንደ ሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘገባ፡፡
ምናልባትም ጫናዎች በርትተው ጆንሰን ስልጣን ሊለቁ የሚችሉ ከሆነ ከሊዝ ትረስ እና ከቤን ዋላስ አንደኞቹ ሊተኳቸው እንደሚችሉም እየተነገረ ይገኛል፡፡