ቦሪስ ጆንሰን “ስልጣን እለቃለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ የሩሲያ ባለስልጣናት ደስታቸውን እየገለጹ ነው
ቦሪስ ጆንሰን ለዩክሬን ባደረጉት ድጋፍ በክሬምሊን ሰዎች ጥርስ እንደተነከሰባቸው ይነገራል
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "ጆንሰን አይወድንም እኛም አንወደውም ነበር " ብለዋል
አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የሩሲያ ባለስልጣናት ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየካቲት 24 በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመረቻውን ተከትሎ ፑቲንን ደጋግመው ሲወቅሱ ከነበሩ ዓለም መሪዎች አንዱ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ፑቲንን “ጨካኝ እና ምክንያታዊነት የጎደለው የክሬምሊን አለቃ” በማለት ሲወሩፏቸው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
ከዚህም ባሻገር ብሪታኒያ የዩክሬን ሰዎች ከሩሲያ ኃይሎች የሚሰነዝርባቸውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመቋቋም የሚያስችላቸው ዘመናዊ መሳሪያ እንዲታጠቁ በማድረግ ረገድ የቦሪስ ጆንሰኗ ብሪታኒያ ትልቅ ሚና ስትጫወት ቆይታለች፡፡
በዚህም ቦሪስ ጆንሰንን ጨምሮ የብሪታኒያ መሪዎች በክሬምሊን ሰዎች ጥርስ ሳይነከስባቸው እንዳልቀረ ይነገራል፡፡
በዚህም አሁን ላይ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከስልጣን እለቃለሁ ማለት የሩሲያ ባለስልጣናት እያስደሰተ ይገኛል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "እሱ አይወድንም እኛም አንወደውም ነበር " ሲሉ ተደምጠዋል።
በቦሪስ ጆንሰን ውድቀት ደስታቸው ከገለጹት የክሬምሊን ሰዎች አንዷ የሆኑት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በበኩላቸው፤ የጆንሰን ውድቀት የምዕራቡ ዓለም ውድቀት ምልክት ነው ብለዋል፡፡
ምዕራባውያን በፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ለመግባታቸው ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል ቃል አቀባይዋ፡፡
ዛካሮቫ “ታሪክ ያስተማረን ነገር ቢኖር፤ ሩሲያን ለማጥፋት አትፈልጉ የሚለው ነው፤ ሩሲያ ልትፈርስ አትችልም" ሲሉም ነው የጆንሰን ከስልጣን መውረድ ከሩሲያ ጋር አያይዘው የገለጹት፡፡
ዛካሮቫ፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን “የእራሱ ውድቀት ደራሲ”ሲ ጆንሰንን ቀልደውባቸዋል።