"የኦነግ ታጣቂዎች ከማፊያው የሕወሓት ቡድን ልዩ ኃይል ጋር በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በማድረስ ተሳትፈዋል" - ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ
"የጨፈጨፏቸውን ወታደሮች አስከሬን ራቁት አድርገው እስከ ትናንት እንዳይቀበርሩ አድርገዋል"
የሬዲዮ መገናኛ ዋና ኃላፊው በማፊያው ቡድን ተጠልፈው ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ ጁንታው ጥቃት መፈፀሙን ገልጸዋል
"የኦነግ ታጣቂዎች ከማፊያው የሕወሓት ቡድን ልዩ ኃይል ጋር በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በማድረስ ተሳትፈዋል" - ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ
በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት የማፊያው ሕወሓት ቡድን ልዩ ኃይል፣ የአካባቢው ሚሊሺያ እና በማይታመን መልኩ ደግሞ የኦነግ ታጣቂ ቡድንም ጭምር እንደነበር ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ አስታወቁ።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ውጊያ እየተካሄደባቸው ያሉ የጦር ቀጠናዎችን የጎበኙት ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ፣ የሕወሓት ማፊያ ቡድን በአካባቢው በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሌ/ጄኔራሉ ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን በአካባቢው ባደረጉት ጉብኝት ማፊያው የሕወሓት ቡድን እየተናገረ እንዳለው የሰሜን እዝ ከማፊያው የሕወሓት ቡድን ጋር በማበር የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እየወጋ እንዳልሆነ ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል።
የሰሜን እዝ ፈተና ቢገጥመውም እና እንዲሸረሸር በሆዳሞች ጥረት ቢደረግበትም የዓላማ ፅናት ያላቸው የጦሩ አባላት በጀግንነት የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈልም ጭምር ጁንታውን ቡድን ተፋልመዋል ነው ያሉት።
ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ በሰሜን እዝ ላይ የደረሰውን ጥቃት ሲያብራሩ፣ እዙ በመቐለ በመሸገው ጁንታ አማካይነት ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ ወደ ማጥቃት ከመግባቱ በፊት በሰሜን እዝ ውስጥ የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎችን በመጠቀም ሰሜን እዝን ለማፈራረስ አቅዶ እንደነበር ገልጸዋል።
የወታደሩ ራሽን እና ደመወዝ መላኩን ቀድመው የማረጋገጥ ሥራ ሠርተዋል ያሉት ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ፣ ይህ ከሆነ በኋላ የሰሜን እዝ ከየትኛውም ሠራዊት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖር ሬዲዮ መገናኛውን አቋርጠዋል ብለዋል።
ሌ/ጄኔራል ባጫ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክተው እንደገለጹት፣ በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ሦስት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው መፈጸማቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ተልዕኮዎቹም ሠራዊቱን ከውስጥ ማፍረስ፣ ሠራዊቱን መውጋትና ማዘናጊያ የሽምግልና ስራ መስራት እንደነበር እና ይህንኑ እንደፈጸሙ አብራርተዋል፡፡
ለዚህ ዓላማ መሳካትም ዋና የሬዲዮ መገናኛ ኃላፊው በማፊያው ቡድን መጠለፋቸውን እና ከዚያ በኋላ ጁንታው ጥቃት መፈፀሙን ገልጸዋል።
ግንኙነቱ ከተቋረጠ በኋላ የ20ኛው ክፍለ ጦር አዛዥን ጨምሮ የተወሰኑ የጦር አመራሮችን ማፈናቸውን፣ በተለይም ደግሞ አጋዥ ኃይል የሚባለውን ለ21 ዓመታት የሀገሩን ዳር ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን ሠራዊት ምንም ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጨፍጭፈው አስከሬኑን አውሬ እንዲበላው በማድረግ ዘግናኝ ድርጊት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።
የጨፈጨፏቸውን ወታደሮች አስከሬን ራቁት አድርገው እስከ ትናንትናው ዕለት እንዳይቀበሩ አድርገዋል ያሉት ሌ/ጄኔራሉ፣ በአስከሬኑ ላይ ሲጨፍሩ እንደነበሩም ገልጸዋል።
ከጭፍጨፋ የተረፉ የሰሜን እዝ ወታደሮችን ልብስ አስወልቀው ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ ሠራዊት እንዲቀላቀሉ ማድረጋቸውን፣ ድንበሩን እየጠበቀ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ግን ራቁታቸውን ለሔዱት የሠራዊታችን አባላት ልብስ ማልበሱን መረጃው እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሰሜን እዝ በርካታ ጥፋቶች ቢፈፀምበትም በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ በአሁኑ ሰዓት በእልህ እና ለባንዲራው ባለው ታማኝነት የጠላት ጦርን በተለያዩ ግንባሮች እየደመሰሰ እንደሆነ እና በየቀኑ አዳዲስ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የሞት ድግስ የተደገሰለት የሰሜን እዝ ሁሉንም ድል አድርጎ የሀገር ዳር ድንበርን እያስጠበቀ የትግራይን ሕዝብ ከዚህ ግፈኛ ጁንታ ነፃ ለማውጣት እየሠራ እንደሆነ እና ባንዲራውን ከፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ዘገባው የኢቲቪ ነው፡፡