በሳህል ቀጠና የሚደርሰው የሽብር ጥቃት መጠን በአለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ መሆኑ ተነገረ
በቀጠናው በሽብር ጥቃት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚመዘገበው ሟች ግማሹን እንደሚሸፍን ሪፖርት አመላክቷል

በአካባቢው ጠንካራ መንግስት አለመኖር እና ያልተረጋጋ ፖለቲካ ለሽብርተኝነት መፈርጠም ምክንያት መሆኑ ተገልጿል
የአለምአቀፍ ሽብርተኝነት ማዕከል እንደሆነ የሚነገረው የሳህል ቀጠና የሚደርሱ የሽብር ጥቃቶች በአለም ላይ ከሚደርሱት በቁጥር እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡
የአለም አቀፍ የሽብርተኝነት ደረጃ ማውጫ ይፋ ባደረገው መረጃ በ2015 በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብር ጥቃት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደርሶበት ከነበረው 11 ሺህ ሟች በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስም የሳህል ቀጠና የሟቾች አሃዝ ከ 2019 ጀምሮ ከነበረበት በአስር እጥፍ ጨምሯል፡፡
ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰው የአክራሪ እና አማፂ ቡድኖች በቀጠናው መበራከት እንዲሁም የመፈንቅለ መንግስት እና የወታደራዊ መንግስታት መጨመር ነው፡፡
“ግሎባል ቴሬርዝም ኢንዴክስ ጂቲአይ” ሽብርተኝነትን “መንግሥታዊ ያልሆነ አካል በፍርሃት፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማህበራዊ ዓላማን ለማሳካት የሚፈፀመው ሕገወጥ ኃይልና ጥቃትን እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡
ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ጠረፍ እስከ ምስራቅ የአህጉሪቱ ክፍል የሚዘልቀው የሳህል አካባቢ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ቻድ እና ሞሪታኒያን የመሳሰሉ 10 ሀገራትን ያካትታል፡፡
አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት በሁለት ድርጅቶች ሲሆን በሳህል የአይኤስ ክንፍ እና የአልቃይዳ ቅርንጫፍ በሆነው “ጃማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል ሙስሊም” (JNIM) በተባሉት የሽብር ቡድኖች ነው፡፡
አይኤስ ሳህል እ.ኤ.አ. በ2020 እና በ2021 በቀጠናው ከተፈፀሙት መፈንቅለ መንግስቶች ወዲህ በማሊ የሚቆጣጠረውን ግዛት መጠን በእጥፍ ጨምሯል ፤ በተለይም በምስራቅ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ድንበሮች አቅራቢያ የሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ አድጓል፡፡
ጄኤንአይ ኤም በበከሉ በቀጠናው ተደራሽነቱን ማስፋፋቱን የቀጠለ ሲሆን በተጨማሪም የህጻናት ወታደሮችን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ ተዋጊዎችን በመመልመል ሀይሉን እያጠናከረ ነው፡፡
ግጭት የሽብርተኝነት ዋና አንቀሳቃሽ እንደሆነ የሚጠቅሰው አለም አቀፍ የሽብርተኝነት ደረጃ ሪፖርት የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የአስተዳደር ድክመት ለአማፅያን ቡድኖች እድገት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሆነ ያብራራል፣
በዚህም መሰረት ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ ባለው በዚህ ከፊል በረሃማ አካባቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ በሽብር ከሞቱ 7,555 ሰዎች ውስጥ በቀጠናው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 3,885 ነው፡፡z