“ግሪንላንድን የብሔራዊ እና የአለም አቀፍ ደህንነት ለማስጠበቅ እንፈልጋታለን” - ዶናልድ ትራምፕ
ትራምፕ በትላንትናው ዕለት ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር ግሪንላንድን “በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ” የአሜሪካ አካል እንደሚያደርጓት ተናግረዋል

በጥር ወር የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 85 በመቶ የሚሆነው የግሪንላንድ ህዝብ ወደ አሜሪካ መቀላቀልን ይቃወማል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግሪንላንድን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በመግለጽ ደሴቷን “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ” የአሜሪካ አካል እንደሚያደርጓት ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ ለሁለቱ ምክር ቤቶች በትላንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር “ግሪንላንድን የብሔራዊ እና አለም አቀፍ ደህንነትን ለማስጠበቅ እንፈልጋታለን በአሁኑ ወቅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “የግሪንላንድ ህዝብ የወደፊት እጣፈንታውን የመወሰን መብቱን እናከብራለን ያሉት ትራምፕ ምርጫቸው ከሆነ የአሜሪካ አካል እንዲሆኑ በደስታ እንቀበላቸዋለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአርክቲክ እና በአትላንቲክ ውቅያኖሶች መካከል የምትገኝው የአለማችን ትልቋ ደሴት ግሪንላንድ ከ1979 ጀምሮ የዴንማርክ ራስ ገዝ ግዛት አካል ነች፡፡
ዴንማርክ አሁንም ድረስ የግሪንላንድን የውጭ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትቆጣጠራለች።
አሜሪካ በበኩሏ ሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓን በአጭር ርቀት በምታስተሳስረው ግሪንላንድ ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላት።
ደሴቱ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መገኛ እና በማዕድን የበለፀገ መሆኑ እንዲሁም በአርክቲክ ውስጥ ስትራቴጅያዊ ስፍራ ላይ መገኘቱ የአሜሪካ ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ ሁለቱም ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ግዛቱን ለመሸጥ የቀረበውን ማንኛውንም ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል፤ የዴንማርክ መንግስት የደሴቲቱ ሉዓላዊነት ይቀጥላል ሲል መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በጥር ወር የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ 85 በመቶ የሚሆነው የግሪንላንድ ህዝብ ወደ አሜሪካ መቀላቀልን ይቃወማል።
ከዚህ ባለፈም ትራምፕ ደሴቱን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ዴንማርክ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ በረጅም ርቀት ድሮኖን የሚደረገውን የቅኝት እና የስለላ ስራ ለማጠናከር 400 ሚሊዮን ዶላር መመደቧ ተሰምቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዴንማርካውያን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የአሜሪካዋን ግዛት ካሊፎርኒያ ለመግዛት የበይነ መረብ ዘመቻ ጀምረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሃቪየር ዱቶይት በተባለ ግለሰብ የተጀመረው ዘመቻ በጥቂት ስአታት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን ፊርማ ማሰባሰብም ችሏል፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ የፓናማ ቦይን እንደሚጠቀልሉ እንዲሁም ካናዳ የአሜሪካ 51 ግዛት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።