ፑቲን፤ “ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሙከራ” እንደማይቀበሉ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ገለፁ
ፕሬዝዳንት ዢ፤ ቻይና ከሩሲያ ጋር ለመስራት እንደምትፈልግ ለፑቲን አረጋግጠውላቸዋል
ፑቲን፤ ለቻይናው ፕሬዝዳንት “በዩክሬን ጉዳይ ያንጸባረቁትን ሚዛናዊ አቋም አደንቃለሁ” ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ “ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገው ሙከራ” እንደማይቀበሉ ለቻይናው አቻቸው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ገለጹ።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ቻይናው ዢ ጂንፒንግ የዩክሬን-ሩሲያ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኡዝቤኪስታን መዲና ሳማርካንድ ተገናኝተዋል
ሁለቱ መሪዎች የሻንጋይ የትብብር ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የጎንዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ፑቲን "አንድ የማይታወቅ ዓለም ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች በቅርብ ጊዜ በጣም አስቀያሚ ቅርጽ እየያዙ ነው፤ እናም ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው" ሲሉ ነው ለቻይናው አቻቸው መናገራቸውን ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
የፑቲንን ኃሳብ የሚጋሩትና “የቀድሞ ጓደኛዬን” በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ያሉት ፕሬዝዳንት ዢ በበኩላቸው ቻይና ከሩሲያ ጋር ለመስራት እንደምትፈልግ ለፑቲን አረጋግጠውላቸዋል።
አክለውም ቻይና "በተመሰቃቀለ ዓለም ውስጥ መረጋጋት እና አዎንታዊ ጉልበት ለማስፋፋት ትፈልጋለች " ብለዋል።
በሌላ በኩል መሪዎቹ የዩክሬን አሁናዊ ሁኔታን አንስተው የተወያዩ ሲሆን ፤የቻይናው ፕሬዝዳንት የዩክሬን ጉዳይ እንደሚስስባቸው ለፑቲን መናገራቸውን ሮይተረስ ዘግቧል።
ዢ በዩክሬን ጉዳይ የተለያዩ ስጋቶችና ጥያቄዎች እንደነበራቸው እረዳለሁ ያሉት ፑቲን፤ የቻይናው መሪ በዩክሬን ጉዳይ ያንጸባረቁትን “ሚዛናዊ አቋም” እንደሚያደንቁ ገልጸውላቸዋል።
"ከዩክሬን ቀውስ ጋር በተያያዘ የቻይና ወዳጆቻችንን ላሳዩት ሚዛናዊ አቋም ትልቅ ክብር አለን" ሲሉም ነው ፑቲን ለዢ የገለጹላቸው።
መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳለቸው የሚነገርላቸው መሪዎቹ በኡዝቤኪስታን ፊት ለፊት ሲገናኙ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ የመጀመሪያ ነው ተብሏል፡፡
በተለይም በኮሮና ምክንያት ኩፉኛ የተፈተነችው ሀገር መሪ ለሆኑት ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የመጀመሪያ የባህር ማዶ ጉዞ መሆኑ ነው።
የመሪዎቹ መገናኘት ፤ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዓለም ፊቱን ላዞረባት ሞስኮ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እየተገለጸ ነው።
ሞስኮ እና ቤጂንግ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባለቸው ግንኙነት የቅርብ አጋሮች ሆነው ብቅ ያሉበት አጋጣሚ ተፈጥረዋል።